የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሒ “ፋርማጆ” በአራት ወራት የስልጣን መንበር ቆይታቸው በእስላማዊ የታጣቂ ቡድን፣ አልሻባብ ላይ ጦርነት በማወጅ ቁልፍ የሆነውን ውሳኔ አስተላልፈዋል፡፡
በድርቅ እየተመታች ባለችው ሶማሊያ ቀደም ሲል በፕሬዝዳንቱ ቤተመንግስት አቅራቢያ ሰባት ሰዎችን ሕይወጥ ከቀጠፈው የቦንብ ፍንዳታ ማግስት ነው እርምጃውን ለመውሰድ የሚያስችል ውሳኔ የተላለፈው፡፡
የታጣቂ ቡድኑ አባላት በ60 ቀናት ውስጥ እጅ ከሰጡ በምትኩ የስልጠ፣ የሥራና የትምህርት ዕድሎች እንደሚመቻቹላቸው ፕሬዝዳንቱ የወታደር ልብሳቸው ሆነው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጸዋል፡፡
በየጊዜው የሚከሰተውን የአጥፍቶ መጥፋት የሽብር ጥቃት ለመከላከል የሶማሊያ የጦር ኃይል በተጠንቀቅ ላይ እንደሆነም ፕሬዝዳንቱ አክለው ገልጸዋል፡፡
የደህንነት፣ የምርመራና የፖሊስ ኃላፊዎችን አደረጃጀት በመከለስ ኃይላቸውን እያጠናከሩ እንደሆነም ታውቋል፡፡
እርምጃው በሞቃዲሾና በሌሎች የአገሪቷ ክፍሎች ተግባራዊ እንደሚሆን የአገሪቷ ጠቅላይ ሚንስትር ሐሰን አሊ ካሃይሪ ገልጸዋል፡፡
እንደ ቢቢሲ ዘገባ አዲሱ የደህንነት እርምጃ የተባበሩት መንግስታት፣ የአሚሶምንና የሶማሊያ የጦር ኃይሎችን ለበለጠ የሰላም ማሰከበር ተልዕኮ እንደሚያበረታታ ተገልጿል፡፡