በግብጽ በቤተክርስቲያን ፍንዳታዎች ቢያንስ 44 ሰዎች ተገደሉ

በግብጽ ሁለት ከተሞች ባሉ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናት ላይ በደረሱ ተከታታይ የቦምብ ፍንዳታዎች ቢያንስ 44 ሰዎች ሲሞቱ ከ 100 በላይ ደግሞ ቆሰሉ፡፡

በፍንዳታው የሞቱት እና የቆሰሉት በአሌክሳንድሪያ እና ታታ ከተሞች የሆሳዕናን በዓል በማክበር ላይ የነበሩ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ናቸው፡፡

የመጀመሪያው ፍንዳታ የደረሰው ከካይሮ በስተሰሜን 100 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በምትገኘው ታታ በተሰኘችው ከተማ ትናንት ረፋዱ ላይ ነበር፡፡

በፍንዳታው ቢያንስ 26 ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ 70 ቆስለዋል፡፡

ፍንዳታው የደረሰበት የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን የሆሳዕናን በአል በሚያከብሩ ምዕመናን ተጨናንቆ እንደነበር ተዘግቧል፡፡

በወደብ ከተማይቱ አሌክሳንድሪያ በሰዓታት ልዩነት በደረሰው ሁለተኛው ፍንዳታ ደግሞ ቢያንስ 11 ሰዎች ሲሞቱ 35 ቆስለዋል፡፡

በግብጽ ክርስቲያኖች ላይ ጥቃት እንደሚያደርስ ሲዝት የቆየው ራሱን “እስላማዊ መንግስት” ብሎ የሚጠራው ጽንፈኛ ቡድን ለሁለቱ ፍንዳታዎች ኃላፊነቱን ወስዷል፡፡

ግብጽን በሚቀጥለው ሳምንት ይጎበኛሉ ተብለው የሚጠበቁት የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ጥቃቱን አውግዘውታል- (ዶች ዌለ) ፡፡