ኔዘርላንድ የኤርትራ ባለሥልጣን ጉብኝት እንደሚያሳስባት ገለጸች

 

በኤርትራ በስልጣን ላይ ካለዉ ሕዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ፍትሕ ፓርቲ ጋር ቅርብ ግንኙነት አለዉ የሚባለዉ የኤርትራ ወጣቶች ኮንግረስ ዓመታዊ ጉባዔዉን በኔዘርላንድ ሮተርዳም ከተማ በማካሄድ ላይ መሆኑ ተገልጾአል።

የኤርትራዉ ፕሬዚዳንት የአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ የፖለቲካ አማካሪ አቶ የማነ ገብርአብ በጉባዔዉ ለመገኘት እና ንግግር ለማድረግ ቀደም ብለዉ ባለፈዉ ሰኞ ሆላንድ መግባታቸዉ ታዉቋል።

የኔዘርላንድ መንግሥት ግን በርካታ የኤርትራ ስደተኞች በጥገኝነት በሚኖሩባት ሆላንድ አንድ የኤርትራ መንግሥት  ከፍተኛ ባለሥልጣን ለኤርትራዉያን ስብሰባ ለመገኘት ወደ ሆላንድ መምጣቱ ያሳሰበዉ መሆኑን ባወጣዉ መግለጫ አስታዉቋል።

አቶ የማነ ገብረ አብ የኤርትራ ብቸኛው የፖለቲካ ፓርቲ ሕዝባዊ ግንባር ለዲሞክራሲ እና ለፍትህ ከሐሙስ እስከ ሰኞ ለሚያኪያሂደው የወጣቶች ስብሰባ ኔዘርላንድ ውስጥ ንግግር እንደሚያደርጉ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

የኔዘርላንድ መንግሥት የኤርትራ  የሰብዓዊ መብት ይዞታ እንደሚያሳስበው አስታውቆ የኤርትራ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሀገራቸውን ጥለው ለወጡ በርካታ ኤርትራውያን ንግግር ሊያደርጉ መሆናቸው ደግሞ «አሳፋሪ ነው» ብሏል።

የአቶ የማነ «ገብረአብ ጉብኝት እንደ ግል ጉዳይ የሚታይ ነው» ያለው የኔዘርላንድስ መንግሥት አቶ የማነ ከማንኛውም ባለሥልጣን ጋር እንደማይገናኙ አስታውቋል።

አቶ የማነ ወደ 650 ለሚሆኑ ኤርትራውያን ስደተኞች ንግግር እንደሚያደርጉ የሕዝባዊ ግንባር ለዲሞክራሲ እና ለፍትኅ የወጣቶች ንቅናቄ ማስታወቁን የዜና ወኪሉ አክሎ ጠቅሷል።

የኤርትራ ስደተኞች ኔዘርላንድ ውስጥ ከሶሪያውያን ቀጥለው በቁጥር በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። 

ምንጭ -www.dw.com