ደቡብ ሱዳን አዲስ ህገመንግስት ለማፅደቅ እንቅስቃሴ መጀመሯ ተነገረ

እኤአ  2015 ደቡብ ሱዳን አዲስ ህገ-መንግስት እንድትቀርፅ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ነው ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት እንቅስቃሴ የጀመረችው ፡፡

በሀገሪቱ በተወሰኑ ግዛቶች የተከሰተው ርሃብ አሁን ላይ ከተፈጠረው ግጭት ጋር ተዳምሮ የሀገሪቱን ዜጎች ለከፋ ስቃይ እየዳረገ ባለበት ወቅት አዲስ ህገ መንግስት ለማዘጋጀት መሞከሩ እያነጋገረ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

በቀድሞው የኬንያ የህገመንግስት ጉዳዮች ዋና ስራ አስፈጻሚ ጊቺራ ኪባራ የሚመራው ብሔራዊ የህገመንግስት አርቃቂ ኮሚቴ የመጀመሪያውን የህገመንግስት ረቂቅ ሰነድ ለደቡብ ሱዳን የፍትህና ህገ መንግስት ጉዳዮች ሚኒስትር ፓውሎ  ዋናዊላ አስረክበዋል፡፡

ኪባራ አሁን ላይ በእርሳቸው የሚመራው ኮሚቴ አዲስ ህገመንግስት እንዲረቅ የጋራ መግባባት ላይ ደርሷል፡፡ የህገ መንግስቱ ረቂቅ በቀጣይ በሚካሄዱ ምክክሮች ይበልጥ የሚዳብር ይሆናል ብለዋል፡፡

አሁን ረቂቁን የተመለከቱ ቴክኒካዊ ጉዳዮች የተጠናቀቁ ሲሆን ቀጣዩ የቤት ስራ ረቂቁን አጠናቆ በሀገሪቱ ፓርላማ  ማስፀደቅ ይሆናልም ነው ያሉት፡፡

 ሀገሪቱ የብሄራዊ ህብረቱን የሽግግር መንግስት ከመሰረተች ወዲህ አዲስ ህገመንግስት በመቅረፅ ተግባራዊ እንድታደርግ የተሰጣት የ18 ወራት የጊዜ ገደብ መጠናቀቁ ተጨማሪ ጫናዎችን እንዳይፈጥር ተሰግቷል፡፡

ለህገ መንግስቱ መዘግየትም ሀገሪቱ በተደጋጋሚ የገባችባቸው የእርስ በእርስ ግጭቶችና ይህን ተከትሎ በሀገሪቱ የተከሰተው ርሃብ በምክንያትነት ቢነሳም እንደ ሰላም ስምምነቱ ከሆነ ግን በመጪው ዓመት 2018 ላይ  በሀገሪቱ ምርጫ እንዲካሄድ ቀነ ቀጠሮ ተይዟል፡፡

የደቡብ ሱዳን መንግስት እና ተፋላሚ ኃይሎች ነሃሴ 2015 ላይ የሰላም ስምምነት ቢፈራረሙም ባለፈው አመት ሀምሌ ወር የማቻር እና ኪር ደጋፊዎች በፈጠሩት ተደጋጋሚ ግጭት በስምምነቱ ትግበራ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሮ ቆይቷል፡፡

በዘንድሮ ዓመት በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሠረት በአገሪቱ የተከሰተው  ግጭት ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ ክፍለ አህጉራዊ እና አለም አቀፋዊ ተቋማት እየጣሩ ይገኛሉ። 

ከሁለት  ሳምንት በፊት በደቡብ ሱዳን በተፈጠረው ግጭት በደቡብ ሱዳን በደቡብ ኢኳቶሪያ ግዛት በምትገኘው በፓጃክ ከተማ የመንግስት ወታደሮች እና ተቃዋሚ ታጣቂዎች ባካሄዱት  ጦርነት ከ6 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ኡጋንዳ መሰደዳቸው የተባባሩት   መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች  ጉዳይ  ኤጀንሲ  ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና ምክትላቸው በነበሩት ሪክ ማቻር መካከል የነበረውን ቅራኔ ተከትሎ በተነሳ ግጭት በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ የደቡብ ሱዳን ሰላማዊ ዜጎች ህይወት ሲያልፍ ከ2 ሚሊየን በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከቅያቸው ተፈናቅለዋል፡፡( ምንጭ አፍሪካ ኒውስ ዶት ኮም )