ኤርትራ በክርስቲያኖች ላይ ጭቆናዋን አጠናክራለች

ኤርትራ በክርስቲያን ዜጎቿ ላይ የምታደርሰውን ጭቆና አጠናክራ በመቀጠሏ የክርስቲያን በጎ አድራጊ ድርጅት ድረጊቱን አውግዟል ፡፡

ሪሊዝ ኢንተርናሽናል የተባለው የክርስቲያን በጎ አድራጊ ድርጅት እንደገለጸው አገሪቱ በቅርቡ ቤት ለቤት ባደረገችው ፍተሻ 200 ያህል ክርስቲያኖችን በቁጥጥር ስር አውላለች፡፡

በተለይም ትናንት የሻዕቢያ መንግስት ወታደሮች 33 ክርስትያን እናቶች ከልጆቻቸው በመለየት በጣሊያን ጊዜ የኤርትራ ህዝብ ታስሮ ይሰቃይበት በነበረው ናኩራ የተባለ ደሴት መታሰራቸውን ነው ድርጅቱ ያመለከተው ፡፡

 “የአገሪቱ ባለስልጣናት ቤት ለቤት በሚደርጉት አሰሳ የሉተራን፣ ካቶሊክ፣ የእስልምና ወይም ኦርቶዶክስ እምነት የማይከተሉ ዜጎችን ሕፃናትን ጨምሮ በቁጥጥር ስር ያውላሉ፡፡” ሲሉ ከድርጅቱ ጋር በአጋርነት የሚሰሩት ዶክተር ብርሃኔ አስመላሽ አስታውቀዋል ፡፡

ኤርትራ ክርስቲያን ዜጎቿን ቤት ለቤት በማሰስ የምታደርገው እስራት ድርጊቱ በክርስያኖች ላይ እየደረሰ ያለውን ጭቆና ማሳያ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት  ፡፡

በኤርትራ ክርስተያኖች ላይ በድርጊታቸው ሳይሆን በእምነታቸው ብቻ እንደሚታሰሩና የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትም ሆነ ለፀሎት መሰባሳብ እንዳልቻሉ ዶክተር ብርሃኔ አክለው የገለጹት ፡፡

ድርጅቱ የታሰሩት ክርስቲያኖች እንዲፈቱ በብሪታኒያና አየርላንድ ፊርማ በማሰባሰብ በእንግሊዝ ለሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ ጥያቄውን እንዳቀረበ መረጃው ያመለክታል፡፡

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፓውል ሮቢንሰን በበኩላቸው በተሰባሰበው ፊርማ ክርስቲያኖች እንዲፈቱ የቀረበው ጥያቄ ዜጎቹ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአፋጣኝ እንዲፈቱ የሚጠይቅ መሆኑህን ነው ያመለከቱት ፡፡

 በዚሁ ምክንያትም እስከ አስር ዓመት ያህል የእስር ቤት ቆይታ ያስቆጠሩ ኤርትራውያን ክርስቲያኖች እንዳሉም ጠቁመዋል ፡፡

“ክርስቲያኖቹ የሀገሪቷ ሕግና ሥርዓት አክብረው የሚኖሩ ሆነው ሳለ የኤርትራ መንግስት ግን ነፃነታቸውንና መሰረታዊ የሰው ልጅ መብቶችን እየጣሰ ነው፡፡” ብለዋል፡፡

ኤርትራ በ1994 ዓመተ ምህረት በርካታ የፕሮቴስታንትና ወንጌላዊ እምነት ተከታዮችን እንዳሰረችና የእነዚህን ቤተእምነቶችንም አገልግሎት እንዳይሰጡ ክልከላ አድርጋ እንደነበር ከክርስቲያን ሬዲዮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡