በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ሁሉም አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ኢጋድ ጥሪ አቀረበ

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን /ኢጋድ/ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ግጭትን ለማስቀረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረበ።

የወቅቱ የኢጋድ የሚንስትሮች ምክር ቤት ሊቀመንበርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በመሩት በዚህ ስብሰባ የጅቡቲ፣ የሶማሊያ፣ የደቡብ ሱዳን፣ የሱዳን፣ የኡጋንዳና የቦትስዋና ከፍተኛ ባለስልጣኖች ተካፍለዋል።

ምክር ቤቱ 57 ልዩ መደበኛ ስብሰባ፤ የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖችን ጨምሮ በአገሪቷ ያለውን ግጭት ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲፈቱና ሁሉም ባለድርሻ አካላትም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

አሁን ሁኔታውን እንደመልካም አጋጣሚ በመውሰድ ሁከትን በማውገዝና ተጨባጭ እቅድ በማቅረብ ከዚህ ቀደም የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ሁሉም ወገኖች ሊተገብሩት እንደሚገባ ነውኢጋድ መግለጫ ያመለከተው።

ምክር ቤቱ የደቡብ ሱዳን መንግስትና ተቀናቃኝ ወገኖች  ግጭቶችን በማቆምና ወደ ሰላም በመምጣት ግንኙነታቸውን የሚያድሱበትን ስልትን አስመልክቶ የተቀመጡ ውሳኔዎችን ተግባራዊ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

ቀደም ሲል በሁለቱ ተቀናቃኞች መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት የተደረሰ ሲሆን፤ ይህም በአፋጣኝና ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲደረግ መሠራት እንዳለበት በዚህ ወር መጀመሪያ ሳምንት ላይ የኢጋድ አባል አገሮች መሪዎች ባካሄዱት ልዩ ስብሰባ ላይ አቅጣጫ መቀመጡ ይታወሳል።