የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ የአፍሪካ ህብረት አሳሰበ

በደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ግጭት ቁልፍ ተዋናዮች ላይ ጠንካራ እርምጃ አንዲወሰድ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሐመት ጥሪ አቀረቡ።

ሊቀመንበሩ በሞሪታኒያ ርዕሰ መዲና ናውክቾች ትናንት በተጀመረው 31ኛ የህብረቱ አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት በደቡብ ሱዳን በአሁኑ ወቅት ያለው ሁኔታ በእጅጉ አሳሳቢ ነው።

በሀገሪቱ ያለው የሰብዓዊና የፀጥታ ችግር እየተባባሰ መጥቶ በአሁኑ ወቅት አስቸጋሪ ደረጃ ላይ መድረሱን የገለፁት ኮሚሽነሩ ባለፈው ሳምንት በሁለቱ የሀገሪቱ ተፋላሚ ወገኖች መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ከወዲሁ አደጋ ላይ መውደቁንም ጠቁመዋል።

“በግጭቱ ቁልፍ ተዋናይ የሆኑት አካላት በየጊዜው የሚገቡትን ቃልኪዳን ባለማክበር በድርጊታቸው ተሰልችተናል” ሲሉም ነው ኮሚሽነሩ የተናገሩት።

የዚህ ዓይነቱ ተግባር ከአሁን በኋላ በዝምታ መታለፍ የሌለበት ነው ያሉት የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ፤“ኃላፊነታችንን እንዲቀበሉ ለማድረግ የሚያስችል እርምጃ የምንወስድበት ወሳኝ ወቅት ላይ ነን ” ሲልም አሳስበዋል።

በግጭቱ ዋነኛ የሆኑት ወገኖች የሚገቧቸውን ቃል ኪዳኖች ያከብሩ ዘንድ ግልፅ መልዕክት ሊተላለፍላቸው ይገባል በማለትም የሚደረግ ማዕቀብ ሊኖር እንደሚችል ሊቀመንበሩ ማስጠንቀቃቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና ተቀናቃኛቸው ዶክተር ሪክ ማቻር ባለፈው ሳምንት በሱዳን ካርቱም በተካሄደው የሰላም ድርድር ላይ የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማምተው የነበረ ቢሆንም ከሰዓታት በኋላ ስምምነቱ መጣሱ ተዘግቧል።

ለዚህም ሁለቱ ወገኖች እርስ በእርሳቸው በመወነጃጀል ላይ መሆናቸውም ተመልክቷል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሁለቱ ወገኖች የፖለቲካ ስምምነት ላይ እንዲደረሱ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር እስከተጠናቀቀው ሰኔ ወር ድረስ ቀን ቆርጦላቸዋል።

በዚህ ጊዜ ውስጥ ይህን ማድረግ ከተሳናቸው ግን ማዕቀብ እንደሚከተላቸውም ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸዋል።

ከዚህ ቀደም በሁለቱ ጎራዎች መካከል የተደረሱት የተኩስ አቁም ስምምነቶች በተደጋጋሚ ሲጣሱ ቆይተዋል።

በደቡብ ሱዳን ላለፉት አምስት ዓመታት በቆየው የእርስ በእርስ ግጭት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ለስደት ተዳርጓል።

ከዚህም ሌላ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ ከቀዬው ተፈናቅሏል፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል።

በአሁኑ ወቅት ሰባት ሚሊዮን የሚሆን የሀገሪቱ ዜጋ ደግሞ የሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልገዋል።

ጠቅላላ የህዝብ ብዛቷ 12 ሚሊዮን እንደሚሆን የሚገመተው ደቡብ ሱዳን አዲስ ሀገር ሆና በዓለም ካርታ ውስጥ ከገባች ገና የሰባት ዓመት አድሜ ያስቆጠረች ናት።(ኢዜአ)