ደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንታዊ የሥልጣን ዘመንን የሚያራዝም የህግ ረቂቅ ማውጣቷ ተሰማ

ደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንታዊ የሥልጣን ዘመንን የሚያራዝም የህግ ረቂቅ ማውጣቷ ተገለጸ ።

ሂደቱ የፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም ያቀደ ነዉ ሲሉም የሀገሪቱ አማፂያን አጣጥለዉታል።

የደቡብ ሱዳን መንግስት የፕሬዚደንት ሳልቫኪር ማያርዲትን ፕሬዚደንታዊ የስልጣን ዘመን ለማራዘም የህግ ረቂቅ ስለማወጣቷ ተሰምቷል።

የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሂደቱ ህገወጥ ነዉ በማለት የሀገሪቱን መንግስት አካሄድ የተቃወሙት ቢሆንም መንግስት ግን ፕሬዝደንት ሳልቫኪር ለቀጣይ ተጨማሪ ሶስት አመታት ደቡብ ሱዳንን የሚመሩበትን ሥልጣን ሊያጎናፅፋቸዉ ስለመሆኑ ነዉ የተነገረዉ።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በሀገሪቱ መንግስት የተዘጋጀዉ የህግ ረቂቅ በህገ መንግስቱ የሰፈረዉን ፕሬዝደንታዊ የሥልጣን ገደብ በማሻሻል የፕሬዚደንት ኪርን የሥልጣን ዘመን እስከ 2021 የሚያራዝመዉ እንደሚሆን ይጠበቃል ተብሏል።

የሀገሪቱ የህግ አርቃቂያን እንዳስታወቁት የህግ ረቂቁ ባሳለፍነዉ ሰኞ ለሀገሪቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበ ሲሆን የደቡብ ሱዳን ህግ አዉጪዎች በስፋት ከመከሩበት በኋላም በተያዘዉ የፈረንጆቹ ወርሀ ነሐሴ በይፋ ፀድቆ በህገ መንግስቱ እንደሚካተት ይጠበቃል።

ይህንን ተከትሎ በዶክተር ሬክ ማቻር የሚመራዉ ቀንደኛዉ የሀገሪቱ አማፂ ቡድን አካሄዱ ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን የሚጥስና ህገ ወጥ ነዉ ሲል ኮንኖታል።

የአማፂ ቡድኑ ቃል አቀባይ እንዳሉት የፕሬዚደንት ኪር መንግስት ምንም አይነት ህጋዊ መሰረት በሌለዉ አካሄድ ፕሬዚደንታዊውን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም መሞከሩ ተቀባይነት የሌለዉና በሀገሪቱ ሰላም ለማምጣት የሚደረገዉን ጥረት ገደል የሚከተዉ ነዉ ብለዋል።

እንደ ሀገር ከተመሠረተች ሰባት አመታትን ያልዘለለችዉ ደቡብ ሱዳን ገና በለጋ እድሜዋ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ መዘፈቋ፣ ከሱዳን ተገንጥለዉ ነፃነታቸውን እንኳን በደንብ ላላጣጣሙት የሀገሪቷ ዜጎች ስቃይና መከራን አስከትሏል። 

ሀገሪቷ እኤአ በ2011 ከሱዳን ተገንጥላ ነፃነቷን ካወጀችበት ጊዜ ጀምሮ የሰላም አየር የራቃትና ስቃይና መከራም የበረታባት ሀገር ሆና አሁን ድረስ ቀጥላለች።

ባለፉት አምስት የሰቆቃና የስቃይ አመታት በሀገሪቱ የዘለቀዉ ሁለንተናዊ ቀዉስ ምክንያት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ደቡብ ሱዳናዊያን ለህልፈት ሲዳረጉ፣ ከሶስት ሚሊየን የሚልቁቱ በአንፃሩ የሞቀ ቤታቸዉን ትቶ መሰደድ ግድ ብሏቸዋል። 

ሀገሪቷ ነፃነቷን በተቀዳጀች ማግስት ወደ ለየለት ጦርነት መግባቷ የሀገሪቱን ዜጎችም ብቻ ሳይሆን ጎረቤት ሀገራትንና የቀጠናዉን ህዝብ ስጋት ላይ ጥሏል።

ለዚህም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የልማት በየነ መንግስት ኢጋድ በደቡብ ሱዳን ሰላም እንዲሰፍንና ዜጎቿም የሰላም አየር እንዲተነፍሱ ለማስቻል ሀገሪቱ ወደ ጦርነት ከገባችበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህ ሂደት ደግሞ ኢትዮጵያ ስትጫወት የነበረችዉ ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑ የሚታወቅ ነዉ።

የኢጋድ የሰላም ጥረት እንዲቀጥልና ኢትዮጵያም እየተጫወተች ያለችዉ ሚና ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚፈልጉት ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በደቡብ ሱዳን ውጥንቅጥ ውስጥ ዋነኞቹ ባለድርሻ አካላትን በአዲስ አበባ ፊት ለፊት አገናኝተዉ ማወያየታቸዉም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። 

ኢጋድ በደቡብ ሱዳን ያለው የእርስ በርስ ጦርነት እንዲቆምና በሀገሪቱም ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ለማስቻል ዋነኞቹ ተዋናዮች የመፍትሄ አቅጣጫ እንዲያቀርቡ በማሰብ ለሁለቱም አካላት ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል ሲል የዘገበዉ ሬዉተርስ ነዉ።