የግብጽና የሱዳን መሪዎች በካርቱም ተገናኝተው በጸጥታ ጉዳዮች እና ስጋቶች ላይ ውይይት አደረጉ

የግብጽና የሱዳን መሪዎች በካርቱም ተገናኝተው አካባቢያዊ በሆኑ የጸጥታ ጉዳዮች እና ስጋቶች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡

የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲና የሱዳኑ አቻቻው ኦማር ሀሰን አልበሽር ካርቱም በሚገኘው ፕሬዝዳንታዊ ቤተ መንግሥት ተገናኝተው ውስጥ ያደረጉት ውይይት የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን የሚያሳድጉ፣ የተለያዩ የጋራ የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን መሰረት ያደረጉ እና አካባቢያዊ እድገትን ለማሻሻል የሚጠቅሙ ነጥቦችን ትኩረታቸው ማድረጋቸውን የሱዳን ባለስልጣናትን ዋቢ ያደረጉ ምንጮች ጠቅሰዋል፡፡

በሱዳን የግብጽ አምባሳደር እንደተናገሩት የመሪዎቹ ምክክር በቀይ ባህር ዙሪያ ያንዣበቡ የጸጥታ ጉዳዮችን እና ስጋቶችን ጨምሮ በደቡብ ሱዳን ሰላምን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት እና በሊቢያ የነበረው ቀውስ የመወያያ ነጥቦች እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዝዳንት አልበሽር ከወይይቱ በኋላ ይፋ ያደረጉት መረጃ እንደሚያመለክተው በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚደረገው የንግድ እና የጉዞ ጉዳዮች ላይ እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን ማስወገድ በሚቻልባቸው ነጥቦች ላይ ከፕሬዝዳንት አብዱል ፈታ አልሲሲ ጋር ተስማምተዋል፡፡

በርካታ ጉዳዮች ዙሪያ ስንነታረክ ብዙ ጊዜያትን አጥፍተናል ያሉት ፕሬዝዳንት አልበሸር አሁን ላይ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እየተሻሻለ መጥቷል ብለዋል፡፡ ይሄንንም አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት፡፡

የግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታ አልሲሲ በበኩላቸው እሳቸው በሱዳን ያደረጉት ጉብኝት አላማ ያደረገው በካይሮ እና በካርቱም መካከል የተቀናጀ ስትራቴጂካዊ ፍላጎትን መደገፍንና በጋራ መስራትን መሰረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ሱዳን አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የጸጥታ ችግሮች ይፈቱ ዘንድ እያደረገች ያለችውን አስተዋጾ በማድነቅ የደቡብ ሱዳንን የሰላም ጉዳይ በተመለከተ ከአልበሽር ጎን እንደሚቆሙ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ገልጸዋል፡፡

መሪዎች ሁለቱ ሀገራት ያቋቋሟቸው የጋራ ኮሚቴዎች እያከናወኑ ያሉትን የሥራ እንቅስቃሴና መሰናክሎችን ለመፍታት እየሄዱ ያሉባቸውን መንገዶች ገምግመዋልም ነው የተባለው፡፡
አልሲሲ ለሁለተኛ ጊዜ የፕሬዝዳንትነት ዘመን ከተመረጡ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ስልጣን ከመጡ ደግሞ ለ5ኛ ጊዜ በካርቱም ለሁለት ቀናት የሚዘልቅ ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

የግብጽ የልዑካን ቡድን ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር፣ የመከላከያና የውሃ ሀብት ሚንስትርና መስኖ እና ግብርና ሚኒስትሮች ያካተተ መሆኑን የዘገበው አሽራቅ አል አውሳት የተሰኘው ድረ ገጽ ነው፡፡