የሶማሊያው ፕሬዚዳንት በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ መጠየቃቸውን የጅቡቲ አምባሳደር ተቃወሙ

በሶማሊያ የጅቡቲ አምባሳደር የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሞሀመድ አብዱላሂ ሞሀመድ በኤርትራ ያካሄዱትን ይፋዊ የስራ ጉብኝት ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ አስተላልፎ የቆየውን ማዕቀብ እንዲያነሳ ያነሱትን ጥያቄ ሀገራቸው በጽኑ እንደምትቃወም አስታውቀዋል፡፡

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሀመድ አብዱላሂ ሞሀመድ ለሶስት ቀናት በኤርትራ መዲና አስመራ ባካሄዱት ጉብኝት የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት እ.አ.አ በ2009 በሶማሊያ ያሉ እስላማዊ ሚሊሻዎችን ይደግፋል በሚል በኤርትራ መንግስት ላይ ያስተላለፈውን የኢኮኖሚ ማዕቀብ እና የጦር መሳሪያዎች እገዳ እንዲያነሳ ጠይቀዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም በኤርትራ ላይ የተላለፈው ማዕቀብ መነሳቱ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ትብብር የበለጠ እንደሚያሳድገው ጠቁመዋል፡፡

በአፍሪካ ቀንድ እያደገ የመጣ ስትራቴጂካዊ አቅም ያላት ሀገር ጅቡቲ ባሳለፍነው ሳምንት የሶማሊያው ፕሬዚዳንት በኤርትራ ያካሄዱትን ይፋዊ የስራ ጉብኝት ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኤርትራ ላይ አስተላልፎ የቆየውን ማዕቀብ እንዲያነሳ ያነሱትን ጥያቄ ሀገራቸው በጽኑ እንደምትቃወም አስታውቃለች፡፡

የፕሬዝዳንት ሞሀመድ ሀሳብ ጅቡቲን አስቆጥቷል፡፡ ጅቡቲም ይህ ሀሳብ እንዳልተዋጠላት የምትገልጸው ኤርትራ በሁለቱ ሀገራት መካከል አከራካሪ የሆነውን እና ጅቡቲ ግዛቴ ነው ብላ የምታስበውን የዱሜራ ደሴቶችን ይዛለች ከዚህም ባሻገር ከአስር በላይ ጅቡቲያውያንን አስራለች የሚሉ ምክንያቶችን በዋቢነት በማንሳት ነው፡፡

በሶማሊያ የጅቡቲ አምባሳደር አደን ሀሰን አደን ከአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ጋር በነበራቸው ቆይታ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሀመድ አብዱላሂ ሞሀመድ  የሰጡት መግለጫ እጅጉን አስደንጋጭ ነው ሲሉ ገልጸውታል፡፡

እንደ አንድ ሉአላዊት ሀገር ሶማሊያ በአፍሪካ ቀንድ ካሉ ሀገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን የማካሄድ መብት እንዳላት የማያከራክር መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ ነገር ግን ሶማሊያ ኤርትራን ስትደግፍ ማየት በኛ በኩል ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ በሶማሊያ ወይንም በምህጻረቃሉ አሚሶም በሶማሊያ ሰላም ለማስከበር ካሰማራቸው የአምስት ሀገራት ሰላም አስከባሪ ሀይሎች መካከል የምስራቅ አፍሪካዊቷ ቀጭኗ ሀገር ሰላም አስከባሪ ሀይሎች ይገኙበታል፡፡

ለሶማሊያ ሰላም ደማቸውን ያፈሰሱ እና ህይወታቸው የገበሩ ፤ ወንድሞቻቸው በአስመራ የታሰሩባቸው ዜጎቻችን የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን  የተሳሳተ አስተያየት መስማት አያስደስታቸውም ሲሉ አምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡

አምባሳደሩ አክለውም ጅቡቲ በቀጠናው የተጀመረውን ዲፕሎማሲያው  ግንኙነት እንደምትደግፍ የገለጹ ሲሆን ጅቡቲ ከኤርትራ ጋር ያላት ግንኙነት መፍትሄ አላገኝም የሚለውን ሀሳብ ግ በአጽንኦት አንስተዋል፡፡

አምባሳደሩ በመጨረሻም ኤርትራ ከተቆጣጠረችው የዱሜራ ደሴቶች ግዛት እስካልወጣች እና ያሰረቻቸውን ጅቡቲያውያን እስካለቀቀች ድረስ የጅቡቲው ፕሬዝዳንት ኤርትራን የመጎብኘት ሀሳብ እንደሌላቸው አስታውቀዋል፡፡