የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ሀይሎች የሰላም ስምምነት ተፈራረሙ

የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ሀይሎች የመጨረሻውን የሰላም ስምምነት አዲስ አበባ ላይ ተፈራርመዋል።

ተቀናቃኝ ሀይሎቹ በትናንትናው እለት በአዲስ አበባ በተካሄደው 33ኛው የኢጋድ የመሪዎች ስብሰባ ላይ ነው የሰላም ስምምነቱን የተፈራረሙት።

የደቡብ ሱዳን የመጨረሻውን የሰላም ስመምነተም የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና ዋንኛው ተቀናቃኛቸው ሪክ ማቻርን ጨምሮ ሌሎች ተፋላሚ ሀይላት ተፈራርመዋል።

ትናንት በተካሄደው 33ኛው የኢጋድ የመሪዎች ስብሰባ ላይ የተገኙት የወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፥ የመሪዎቹ ስብሰባ የተካሄደው የቀጠናው ሰላም ወደ ተሻለ ደረጃ በደረሰበት ወቅት መሆኑን አንስተዋል።

እንዲሁም ኢጋድ በደቡብ ሱዳን ቀውስ ዙሪያ ላበረከተው የሰላም ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)