ሶማሊያና ጂቡቲ የሰላም አስከባሪ ሀይሎቻቸውን ወደ ደቡብ ሱዳን ሊያሰማሩ ነው

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ኢጋድ ሶማሊያ እና ጂቡቲ የሰላም አስከባሪ ሰራዊት ወደ ደቡብ ሱዳን እንዲያሰማሩ መፍቀዱን አሰታውቋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት ወታደሮች በሀገሪቱ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ሀይሎች መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት እንዲተገበር እና የሰላም ስምምነቱ ፈራሚ አካላትን ደህንነት ማጠናከር አላማው ማድረጉም ነው የተነገረው፡፡

ኢጋድ ያወጣው መግለጫ እንደሚያመለክተው ሶማሊያ እና ጂቡቲ በደቡብ ሱዳን ሰላምን ለማምጣት እየተሳተፉ ያሉ ሀገሮችን ዝርዝር እንዲቀላቀሉ በክፍለ አህጉራዊው ድርጅት የታጩ ሀገሮች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ደርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን አህጉራዊ የደህንነት ሃይልን ለማሰማራት ይረዳ ዘንድ ሱዳን፣ ኡጋንዳ፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ የሰላም አስከባሪ ሰራዊቶቻቸውን ወደ ሀገሪቱ እንዲያስገቡ መጠየቁን የኢጋዱ መግለጫ እንደሚያትት ደይሊ ሞኒተር ዘግቧል፡፡

ኢጋድ ደቡብ ሱዳን እና ህዝቦቿ በሀገራቸው ሰላም መረጋጋት እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማጠናከር በሚያደርጉት ጥረት ከጎናቸው ለመቆም ቁርጠኛ መሆኑንም ነው የገለጸው፡፡

የእርስ በእርስ ጦርነት መታወቂዋ በሆነችው ሀገር ውስጥ የሚገኙት ተቃዋሚ ቡድኖች እና መንግስት የሰላማዊ ህዝቦችን ደህንነት ማስጠበቅ እንዲችሉ እና ሰብአዊ እርዳታዎች ተደራሽ እንዲሆኑ ለማድረግ ዘላቂ የሆነው የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ ኢጋድ ገልጿል፡፡

ሶማሊያ በአፍሪካ አህጉር ከሚገኙ ሀገራት ከፍተኛ የሆነ የደህንነት ስጋት የተጋረጠባት ሀገር ስትሆን የሀገሪቷን ሰላም እና ደህንነት ለማረጋገጥ ብዙ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ሰላም አስከባሪ ሀይል መላካቸው ይታወቃል፡፡

አትዮጵያን ጨምር ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ቡሩንዲ የሰላም አስከባሪዎችን ወደ ሶማሊያ መላካቸው አይዘነጋም፡፡

ሶማሊያም ተራው ዶርሷት የሰላም አስከባሪ ሀይል ወደ ደቡብ ሱዳን ለመላክ መቻሏ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የአካባቢያቸውን ስላም ለማስከበር ያላቸውን ቁርጠኝነት ማሳያ ተደርጎ ሊወስድ ይችላል፡፡ (ምንጭ፤ዴይሊ ሞኒተር