የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአብዬ ተጨማሪ የፖሊስ ቡድኖች እንዲሠማሩ ጠየቀ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአብዬ ተጨማሪ የፖሊስ ቡድኖች እና ልዩ ሃይሎች እንዲሰማሩ ጠይቋል ።

ሱዳን በበኩሏ በድርጅቱ የቀረበላትን የአብዬን ሰላም አስከባሪ ሃይል ድጋሚ የማዋቀር ጥያቄ እንደማትቀበል ገልፃለች፡፡

የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ሐሙስ እለት ባካሄደው ጉባኤ ላይ ሱዳን የአብዬ ሰላም አስከባሪ ኃይል ዳግም እንዲዋቀር ሲል ጠይቋል፡፡

በኒው ዮርክ በተካሄደው ውይይት ላይ በተሠጠው ማብራሪያ የተባበሩት መንግስታት ህግ እና ደንብ እንዲከበር በአካባቢውም ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የፀጥታው ምክር ቤት በአብዬ ግዛት ተጨማሪ የፖሊስ ቡድን እንዲመደብ ሱዳንን ጠይቋል፡፡

ሱዳን ትሪቡን ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው የሚጨመሩት የፀጥታ ቡድኖች በድንበር አካባቢ የሚሠማሩ ሲሆን በአካባቢው ላይ በታጣቂዎች ግጭት እንዳይከሰት ለማድረግ ያለመ ነው፡፡

የፖሊስ ኃይሉ በሶስት ቡድን እና በልዩ ኃይሎች እንደሚዋቀርም ዘገባው ያተተ ሲሆን የተልዕኮው ህግና ደንብ በማስከበር በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ እየጨመረ የመጣውን ወንጀል በመቅረፍ  ዘላቂነት ያለው ሰላም እንዲሰፍን ያግዛል ተብሏል፡፡   

ሱዳን ግን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክርቤት ጥያቄ አልተስማማችም፡፡

በተባበሩት መንግስታት የሱዳን አምባሳደር ኦማር ዳሃብ ፋድል ጥያቄው በአካባቢው ሚሰርያ እና ዲንካ ማህበረሰቦች ላይ የሰፈነውን መልካም ሁኔታ የሚደፈርስ ነው በማለት አጣጥለውታል፡፡

አምባሰደሩ አክለዉም በአብዬ ጉዳይ ላይ በቂ ጥናት እስካልተደረገ ድረስ ተቀባይነት የለዉም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ግጭት በሚነሳባቸው ቦታዎች ላይ ዓለም አቀፍ ስምምነት እስካልተፈፀመ ድረስ አብዬ የሱዳን አካል ሆና እንደምትቀጥል እና ሉአላዊነቷ እንደሚጠበቅ አፅንኦት በመስጠት ተናግረዋል፡፡