የኬንያ ፓርላማ ሴቶች አንድ ሦስተኛ መቀመጫ በሚይዙበት ሁኔታ ላይ እየተከራከረ ነው

የኬንያ ፓርላማ ሴቶች የፓርላማውን አንድ ሶስተኛ መቀመጫ መያዝ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ እየተከራከረ ነው፡፡

አሁን ላይ በሀገሪቱ ሴቶች ያላቸው የፓርላማ መቀመጫ ብዛት ከ23 በመቶ እንደማይበልጥ ታውቋል፡፡

የኬንያ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ሴቶች ያላቸው ውክልና አንድ ሶስተኛ እንዲሆን በሚያስችለው መመሪያ ላይ እየተከራከረ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

ሓሳቡን ደግፈው እየሞገቱ ያሉት የፓርላማ አባላት ሴቶች በሀገሪቷ ህግ መወሰኛ ምክር ቤት ውስጥ የተሻለ ውክልና ቢያገኙ ከዚህ በፊት በሀገሪቱ የተፈጠሩ ስህተቶች እንዳይደገሙ ይረዳል ሲሉ ይሞግታሉ፡፡

በኬንያ የላይኛው እና የታችኛው ምክር ቤት ውስጥ ሴቶች ያላቸው የፓርላማ መቀመጫ ቁጥር 23 በመቶ እንደሆነ ይነገራል፡፡

ይህ ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገራት ካላቸው ሴት የፓርለማ አባላት ቁጥር ጋር ሲነጻጸር አማካኝ ላይ ቢገኝም ከጎረቤት አገሮቿ ሩዋንዳ፣ ኢትዮጵያ እና ቡሩንዲ አንጻር ግን አነስተኛ እንደሆነ የሮይተርስ ዘገባ ያሳያል፡፡

በኬንያ እኤአ ከ2010 ጀምሮ ተግባራዊ የሆነ ሕግ ተመራጮችም ሆነ ተቃዋሚ የፖለቲካ አካላት ያላቸው የጾታ ስብጥር ሲታይ ተመሳሳይ ጾታ ከሁለት ሦስተኛ መብለጥ እንደሌለበት ቢደነግግም ሁኔታውን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችሉ ዘዴዎችን አያስቀምጥም፡፡

የፓርላማ አባል በሆኑት ኤደን ባሬ ዱዋሌ የቀረበው አዲሱ የህግ ረቂቅ እቅድ በፓርላማ  ያለው የወንድና ሴት መቀመጫ ቁጥር ህገ መንግስቱ በሚፈቀደው መልኩ ካልሆነ ቁጥሮችን ለማሟላት ይቻል ዘንድ ልዩ መቀመጫዎችን በሴቶች  መሙላት የሚያስችለውን ዘዴ እየተቀየሰ እንደሆነም ተናግሯል፡፡

በታሪክ ተመዝግበው የሚገኙ በሴቶች ላይ የተፈጸሙትን ኢፍትሃዊ ተግባራትን ማስተካከል እንፈልጋለን፤ይህንን ለማድረግ ደግሞ የሀገራችንን ሴቶች አቅም ማጎልበት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ልንሰራ ይገባል ብለዋል ።

ሴቶችን መሪ የሚሆኑበት እና ውሳኔ የሚሠጡበትን ኃላፊነት በህግ አግባብ ማዘጋጀት አለብን ሲሉ ሀገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኘው የጁብሊ ፓርቲ ተወካይ ተናግረዋል፡፡

የኬንያ ምጣኔ ሃብት ባለፉት አሥር አመታት በአማካይ በ5 በመቶ እድገት ቢያስመዘግብም ሴቶችና ልጃገረዶች ያላቸው ማህበራዊ ኢኮኖሚ እና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ግን አነስተኛ መሆኑ ይነገራል፡፡

የኬንያ ብሔራዊ ስታስቲክስ ቢሮ ባወጣው መረጃ መሠረት ሴቶች በመደበኛ ዘርፍ ላይ ተቀጥረው ከሚሰሩት 2ነጥብ5 ሚሊዮን ሰዎች ውስጥ ሴቶች ያላቸው ተሳትፎ አንድ ሦስተኛ ብቻ ነው፡፡

በተጨማሪም 80 በመቶ የሚሆነውን የኬንያ የእርሻ ላ ሥራዎችን ሴቶች ቢያከናውኑም አንድ በመቶ ብቻ የሚሆነውን የሀገሪቱን የእርሻ መሬት ብቻ በባለቤትነት የማስተዳደር እጣፈንታቸው መሆኑ ዋቢ  የተደረጉ መረጃዎችን ይገልጻሉ ፡፡

የሥርዓተ-ፆታ ባለሙያዎች በከፍተኛ ሥልጣን ላይ የሚገኙ ሴቶች ድምጽ ተጨባጭ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል በመጠቆም ሴቶች በኅብረተሰቡ ደረጃ በደረጃ የሚደርስባቸውን በደል እና መድልዎ በእኩልነት ለመዋጋት የሚረዱ ፖሊሲዎችን እና ህጎችን ለማርቀቅ ይረዳልም ብለዋል፡፡

አሁን የቀረበው ረቂቅ መመሪያ በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታና በተቃዋሚ መሪው ራይላ ኦዲንጋ ድጋፍ ማግኘቱ ቢነገርም ተጨማሪ የፓርላማ ወንበሮችን መፍጠር ለተመራጮቹ ደመወዝ መክፈል ይቻል ዘንድ የሀገሪቱ ግብር ከፋዮች በሚሊዮን ብሮችን የሚቆጠሩ ተጨማሪ የበጀት አስዋፅኦ እንዲቀረጡ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል የፓርላማ አባላቱ በመከራከሪያ ነጥባቸው እያንጸባረቁ ነው፡፡

ሌሎች ደግሞ አሁን በሥልጣን ላይ የሚገኙ ፖለቲከኛ ሚስቶች እና ጓደኞች ባላቸው ቅርበት ሳቢያ የፓርላማ ወንበርን ሊያገኙ ይችላሉ የሚል ስጋት ደቅነዋል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡