ሱዳን ላሰፈረቻቸው ስደተኞች ተጨማሪ ፈንድ እንዲያደርግ የአውሮፓ ህብረትን ጠየቀች

ሱዳን በሃገሯ ለሚኖሩ የተለያዩ ሃገራት ስደተኞች ተጨማሪ ፈንድ እንዲያደርግ የአውሮፓ ህብረትን ጠይቃለች፡፡

የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤል ዲርዴሪ አህመድ ከአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳዮች እና የደህንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ ፌዴሪካ ሞግሄሪኒ ጋር በብራሰልስ ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡

የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ባቢከር አል ሳዲቅ በሰጡት መግለጫ ሁለቱ ባለስልጣናት በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን እና በክልሉ ወቅታዊ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

በደቡብ ሱዳናውያን ስደተኞች እና በሃገሪቷ በሚከሰተው ግጭት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የሚፈናቀሉ ዜጎች ሰብአዊ መብት ጉዳዮችም የውይይታቸው አካል ነበር፡፡

በዚህም የሱዳን መንግስት ለነዚህ ስደተኞች እና ተፈናቃዮች ተጨማሪ እርዳታ ያስፈልግቸዋል ሲል ነው የአውሮፓ ህብረትን የጠየቀው፡፡

ምክንያቱም ደግሞ እስካሁን ድረስ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስደተኞቹ ከሚያስፈልጋቸው ጠቅላላ ሰብአዊ እርዳታ 37 በመቶ ብቻ የሚሆነውን  እየሸፈነ እንደሆነ ነው በተደጋጋሚ የሚገለጸው፡፡

ሞግሄሪኒ በበኩላቸው ሱዳን እያደረገችው ያለውን ተግባር በማድነቅ የአውሮፓ ህብረት በተለያዩ መንገዶች ወደ ሱዳን ለገቡ ስደተኞች የሰብአዊ እርዳታ የሚሆን ተጨማሪ 20 ሚሊዮን ዩሮ ፈንድ እንደሚፈቅድ ገልጸዋል፡፡

የሱዳን የስደተኞች ስታቲክስ ኮሚሽን ሪፖርት እንደሚያመላክተው ከኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ቻድ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሲዳን፣ የመን እና ሶሪያ የመጡ ስደተኞች 2 ሚሊዮን እንደሚሆኑ ያመላክታል፡፡

ከነዚህም ውስጥ 110 ሺ ኤርትራዊያን ስደተኞች፣ 400 ሺ ደቡብ ሱዳንያዊያን፣ 100 ሺ የሚሆኑ ሶሪያውያን ስደተኞችን እያስተናገደች ትገኛልች፡፡  እንደ የተባበሩት መንግስትት ድርጅት መረጃ፡፡

በተጨማሪም በአሁኑ ሰአት ከ500 ሺ በላይ የሚሆኑ በሱዳን የሚገኙ ደቡብ ሱዳንያዊያን ስደተኞች ደግሞ አፋጣኝ የሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ነው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት የሚያመላክተው፡፡ /ሱዳን ትሪቢዩን/