ኢጋድ በደቡብ ሱዳን የተፈጸመውን ጥቃት አወገዘ

የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድር ዙሪያ ባወጣው መግለጫ በሀገሪቱ የተፈጸመውን ጥቃት አውግዟል፡፡  

መግለጫው ታህሳስ 9 ቀን 2011 ዓ.ም በደቡብ ሱዳን የሚገኙ ታጣቂዎች በደቡብ ሱዳን የተሠማራውን ዩሰላም አስከባሪ ታዛቢ ቡድን ላይ በፈጸሙት እስራት እና እንግልት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማው ገልጿል።  

እንደዚህ አይነት ዘግናኝ ጥቃት ከዚህ ቀደም በሽግግር መንግስት እና በደቡብ ሱዳን ተቃዋሚ ኃይሎች የተፈረመውን የሰላምና የተኩስ ማቆም ስምምነት መጣስ ብቻ ሳይሆን የግለሰቦችን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ጭምር ነው ብሏል ኢጋድ በመግለጫው፡፡

ክስተቱ የታሰበውን የሽግግር መንግስትና ብሄራዊ አንድነት ለማምጣት የተጀመረውን ስራና መንፈስ የሚጻረር መሆኑም ተገልጿል።

ሁኔታው ለኢጋድ አባል ሀገራት እና ለሌሎች ተቀማጭነታቸው በሱዳን ላደረጉ የደህንነት እና የተኩስ አቁም ተቋማት ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል እንደሆነ ገልጸዋል። 

የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የስምምነቱ መጣስን በጥብቅ የኮነነ ሲሆን የሽግግር መንግስቱ በአፋጣኝ ምርመራ እንዲያደርግ፣ ፈጻሚዎቹን እንዲለይ፣ ቀጥታ ግንኙነት ያላቸውን ኃላፊዎቻቸው ለፍትህ እንዲቀርቡ ለፈጸሙት ወንጀል የሚመሩትን ሀገር እና ህዝብን ባስቸኳይ ይቅርታ ጠይቀው ለምክር ቤቱ እንዲያሳውቁ ሲል ገልጿል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ ለተፈጸመው ስምምነት ፊርማቸውን ያኖሩትም ሆነ ያላኖሩ አካላት ለኢጋድ ምክር ቤትና ለሌሎች የሰላም አስከባሪ ተቋማት ምርመራ እንዲያደርጉ ሙሉ ትብብር እንዲያደርጉና የድርጊቱ ፈጻሚዎች ተጠያቂ እንደሚሆኑ ገልጸዋል። (ምንጭ፡-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጽህፈት ቤት)