በሱዳን የተቀሰቀሰው ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው

በሱዳን የዳቦና ነዳጅ ዋጋ ጭማሪን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ አሁንም እየቀጠለ መሆኑ ተገለጸ ።

በሀገሪቱ የሚገኙ ሀኪሞችም በፕሬዝዳንት ኦማር አል-በሽር ላይ ጫና ለማሳደር ተቃውሞውን የተቀላቀሉ ሲሆን መንግሥት ተቃውሞውን ለማዳፈን እያካሄደ ያለውን የእስር ዘመቻ እንዲያቆምም ጥሪ ቀርቧል፡፡

ካለፈው የፈረንጆቹ አመት ጀምሮ በሱዳን የተለያዩ ሸቀጦች ዋጋ በእጥፍ መጨመሩ ይነገራል፡፡ የሀገሪቱ የዋጋ ግሽበት ሰባ በመቶ መድረሱ የተጠቆመ ሲሆን የመገበያያ ገንዘብ ምንዛሬ አሽቆልቁሏል፡፡

ለኢኮኖሚው ማሽቆልቆል እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱ ጉዳዮች መካከል እኤአ በ1990ዎቹ አሜሪካ የአልበሽር መንግሥት ሽብርተኞችን ይደግፋል" በሚል እስከ 2017 ድረስ ጥሎት የነበረው የንግድ ማዕቀብ ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ሌላው እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው ደግሞ ደቡብ ሱዳን በ2011 ከሱዳን ስትገነጠል የሀገሪቱን አብላጫ የነዳጅ ሀብት ይዛ መገንጠሏ ነው፡፡

በሱዳን የዳቦና የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን ተከትሎ የተቀሰቀሰውና አምስት ቀናትን ያስቆጠረው ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች በሱዳን መዲና ካርቱም መንገድ በመዝጋት ከፖሊሶች ጋር ግጭት ፈጥረዋል፡፡ፖሊስም ተቃዋሚዎችል ለመበተን አስለቃሽ ጭስ መጠቀሙን ዘገባው አመላክቷል፡፡ 

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ 22 ሰዎች መገደላቸው ቢነገርም መንግሥት ግን የሟቾች ቁጥር ስምንት ብቻ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ይህንኑ ተቃውሞ ተከትሎ በፕሬዝዳንት ኦማር አል-በሽር ላይ ጫና ለማሳደር በሀገሪቱ የሚገኙ ተቃዋሚዎች ተቃውሞውን ተቀላቅለዋል፡፡

መንግሥት ተቃውሞውን ለማዳፈን 'ናሽናል ኮንሰንሰንስ ፎርስስ' የተባለውን የተቃዋሚ ኃይሎች ጥምረት የሚመሩ 14 አመራሮችን ማሠሩን የጥምረቱ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡ቃል አቀባዩ አመራሮቹ በአስቸኳይ እንዲፈቱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከአንድ ዓመት ስደት በኋላ በቅርቡ ወደ ሱዳን የተመለሱትና ኡማ የተሰኘውን ተቃዋሚ ፓርቲ የሚመሩት ሳዲቅ አል-ማዲ በበኩላቸው ሕዝቡ ወታደራዊ ጭቆና እንዳስመረረው በመግለጽ የአል-በሽር አስተዳዳር በሰላማዊ መንገድ ሥልጣኑን መልቀቅ አለበትም ብለዋል።

 

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት የሱዳን ሰላም ለደቡብ ሱዳንም ሆነ ለቀጠናው ሰላም አስፈላጊ በመሆኑ ድጋፋቸው እንደማይለያቸው  ለኦማር ሀሰን አልበሽር በስልክ ገልጸውላቸዋል፡፡

ሱዳንም የተከሰተውን ግጭት ለማብረድም እንደምትሰራ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል ። (ምንጭ: ቢቢሲ )