ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ከተባበሩት መንግስታት፣ ከአፍሪካ ህብረትና ከኢጋድ ተወካዮች ጋር ውይይት አካሄዱ

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ  ከተባበሩት መንግስታት፣ ከአፍሪካ ህብረትና ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስት ተወካዮች ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡

ተወካዮቹ በደቡብ ሱዳን የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ሲሆን የጉብኝቱ አላማም ለሰላም ስምምነቱ ስኬታማነት ያለውን ቀጠናዊና አለም አቀፋዊ ድጋፍ ለማሳየት መሆኑ ተነግሯል፡፡

በደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ሀይሎች መካከል ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት መስከረም ወር ላይ በተካሄደው የሰላም ስምምነት ጥምር መንግስት ለመመስረት ለግንቦት 12 ቀን 2019 ቀጠሮ ተይዞ ነበር፡፡

የአማጺያኑ መሪ ሬክ ማቻር በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ አዲስ ጥምር መንግስት እንዲመሰረት ጥሪ ቢያቀርቡም ፕሬዘዳንት ሳልቫ ኪር መንግስት የተፋላሚ ሃይሎችን ትጥቅ ማስፈታት፣ የተለያዩ የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎችን ማሰልጠንና ውህደት መፍጠር ባለመቻሉ ለአንድ ዓመት መራዘም እንደሚገባው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት በደቡብ ሱዳን ተቃዋሚ ሀይሎች መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተፈጻሚ ለማድረግ እየተከናወኑ ስላሉ ስራዎችና በቅርቡ ስለተራዘመው የሽግግር ጊዜ በሚመለከት ከተባበሩት መንግስታት፣ ከአፍሪካ ህብረትና ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስት  ተወካዮች ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡

ተወካዮቹ በደቡብ ሱዳን የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ሲሆን የጉብኝቱ አላማም ለሰላም ስምምነቱ ስኬታማነት ያለውን ቀጠናዊና አለም አቀፋዊ ድጋፍ ለማሳየት መሆኑ ተነግሯል፡፡

ተወካዮቹ ከፕሬዝዳት ሳለቫኪር ጋር በነበራቸው ቆይታ የሀገሪቱ ተፋላሚ ሀይሎች የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ እያከናወኑ ላሉት ተግባር ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ የተጀመሩ ስራዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ሀላፊ ጄን ፒር ላክሮኢክስ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ስምምነት ሂደቱን እንደሚደግፍ አስታውቀዋል፡፡

የሰላም ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ለደቡብ ሱዳን ህዝብ ጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኒያል ዴንግ ጥምር መንግስት ለመመስረት የሚያስፈልገው ጊዜ የተራዘመው መጪው ጊዜ ዝናባማ ወቅት መሆኑን ተከትሎ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቋቋም በማሰብ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

(ምንጭ፡-ሱዳን ትሪቡን)