የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ፍላጎት ዴሞክራሲን ማስፈን መሆኑን ገለጸ

የሽግግር ምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ሌተናንት ጄነራል ሃምዳን ዳግሎ የሃገሪቱ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኦማር አል በሽር የታሰሩበት ኮበር ማረሚያ ቤትን በጎበኙ ወቅት የሽግግር ምክር ቤቱ ዲሞክራሲን ማስፈን እንጂ ስልጣን ላይ የመቆየት ፍላጎት የለውም ብለዋል፡፡

ምክር ቤቱ ከ”ፍሪደም ፎር ቼንጅ” ከተባለው ተፎካካሪ ፓርቲ ጋር ያለው ግንኙነት መልካም እንዲሆን እየመከርን ነው ብሏል፡፡

በፍሪደም ፎር ቼንጅ አነሳሽነት የተጀመረው የሱዳናውያኑ ተቃውሞ በሃገሪቱ ወታደር ባይደገፍ ኖሮ የኦማር አልበሽር አስተዳደር ባልተወገደ ነበር ያሉት የሽግግር ምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ፍሪደም ፎር ቼንጅ ከተባለው የመንግስት ተፎካካሪ ፓርቲ ጋር ያለንን ግንኙነት መልካም እንዲሆን እየመከርን ነው ብለዋል፡፡

ፓርቲው ፍትሃዊ ባልሆነ መልኩ እየታየን ነው ማለቱን ግን ትክክል አይደለም ሲሉም ተችተዋል፡፡

ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ወታደሩ ወደ ካምፑ እንዲመለስ እና ሁኔታዎችን ብቻቸውን የመቆጣጠር ፍላጎት እያሳዩ ነው ብለዋል ምክትል ፕሬዝዳንቱ፡፡ ቢሆንም ግን በሃገሪቱ ዲሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር እስኪካሄድ ድረስ ጦሩ ወደ ካምፕ አይመለስም ብለዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ከተፎካካሪ ቡድኖች ጋር ተወያይቶ በተለይም ከዲክላሪሽን ኦፍ ፍሪደም አንድ ቼንጅ ፓርቲ ጋር በቁልፍ ጉዳዮች ሳይስማማ የቀረው ምክርቤቱ ተደጋጋሚ ውይይቶችን ቢያካሂድም ተቃውሞዉን የሚያረግብ መፍትሔ ግን ማምጣት አልቻልም፡፡