ኡጋንዳ የሩዋንዳ ወታደሮች ክልሌን ጥሰዉ በመግባት ንፁሀን ዜጎቼን ገድለዋል አለች

ኡጋንዳ የሩዋንዳ ወታደሮች ከልሌን ጥሰዉ በመግባት ሁለት ንፁሀን ዜጎቼን ህይወት ቀጥፈዋል ስትል ከሳለች፡፡

በርካታ ኡጋንዳዊያን  ይህንን ድርጊት በመቃወም ላይ ሲሆኑ ድርጊቱ የሩዋንዳ ወታደሮችን ስርአት አልበኝነት ያመላከተ ከመሆኑም በላይ  በሁለቱ ጎረቤት ሀገራት መካከል ያለዉን መልካም ግንኙነት ያበላሻል ብለዋል፡፡

የኡጋንዳ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደገለጹት ሁለት የሩዋንዳ ወታደሮች በኡጋንዳ ደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ በሚገኘዉ ሩኪጋ ግዛት ከገቡ በኋላ ባልታጠቁ ሁለት ሲቪሎች ላይ ተኩስ በመክፈት ህይወታቸዉ እንዲያልፍ አድርገዋል ብለዋል፡፡

ድርጊቱ ጸብ አጫሪነት ከመሆኑ ባሻገር አሳሳቢ ነዉ ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትሩ ኡጋንዳ ይህን በጥብቅ ታወግዛለች ብለዋል፡፡

የሩዋንዳዉ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪቻርድ ሲዝቤራ በበኩላቸዉ አካባባቢዉ የተለያዩ ችግሮችን ሊያሥተናግድ የሚችል ቦታ ቢሆንም ወታደሮቻችን የኡጋንዳን ድንበር ጥሰዉ ሊገቡ አይችሉም ብለዋል፡፡

መሰል ሀሰተኛ ዜናዎች መበርከታቸዉን በመጠቆም ለጉዳዩም ትልቅ ትኩረት በመስጠት እንከታተለዋለን ሲሉ በቲዉተር ገፃቸዉ አስፍረዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት ካለፈዉ የካቲት ወር ጀምሮ  ያላቸዉ  ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ግንኙነት  እየሻከረ የመጣ ሲሆን ኡጋንዳ  በሩዋንዳ በኩል ወደ  ካቱና ግዛት የምያስገባዉን ድንበር ዘግታለች፡፡

የዑጋንዳ ዜጎችም ወደ  ጊካሊ እንዳይገቡ የሐገሪቱ ባለስልጣናት አግደዋል  ፡፡

የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረዉን አለመግባባት ማስተካከል ቢፈልጉም በኡጋንዳ በኩል ግን በጎ ምላሽ እንዳላገኘ የአልጀዚራ ዘገባ ያሳያል፡፡