የማላዊ ፕሬዝዳንት ፒተር ሙታሪካ ዳግም ተመረጡ

የማላዊ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባደረገው ማጣራት ግንቦት 15 በተካሄደው አገራዊ ምርጫ ፕሬዝዳንት ፒተር ሙታሪካ ዳግም መመረጣቸው ታወቋል፡፡

የ78 ዓመቱ ፒተር ሙታሪካ ዳግም የተመረጡት 38.5 በመቶ ድምፅ በማግኘት በጠባብ ልዩነት ነው ተብሏል፡፡

ምርጫውን በሁለተኝነት ያጠናቀቁት ላዛረስ ቻክዌራ ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል ውጤቱ ሳይገለፅ በፊት ማጣራት እንዲደረግ ጠይቀው ነበር፡፡

በዚሁ መሰረት የአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የማጣራት ስራ ሲሰራ ቆይቶ በትናንትናው ዕለት የምርጫው ውጤቱ እንዲገለፅ አዟል፡፡

ከፍርድ ቤት ማጣራት በኋላ የማላዊ ምርጫ ቦርድ እንዳስታወቀው ዴሞክራቲክ ፕሮግሬሲቭ ፓርቲን የሚመሩት ፕሬዝዳንት ሙታሪካ በ38.5 በመቶ በ159 ሺህ ጠባብ የድምጽ ብልጫ አሸንፈዋል፡፡

ማላዊ ኮንግሬስ ፓርቲን የሚመሩት ቻክዌራ ምርጫውን በ35.4 በመቶ ድምፅ ሁለተኛ ሆነው አጠናቀዋል፡፡ ቻክዌራ በባለፈው ምርጫም በሁለተኛነት ነበር ያጠናቀቁት፡፡

የፕሬዝዳንት ሙታሪካ ምክትል የሆኑት ሳውሎስ ቺሊማ በምርጫው 20 በመቶ ድምፅ በማግኘት ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል፡፡

ማላዊ ነፃነትዋን ያገኘችው በ1956 ሲሆን፣ አገሪቱ ከዚያ ወዲህ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ስታካሂድ ያሁኑ ለ6ኛ ጊዜ ነው ተብሏል፡፡

(ምንጭ፡-ቢቢሲ)