የኬንያ መንግሥት ከሶማሊያ ጋር የሚያዋስነውን ድንበር ዘጋ

የኬንያ መንግሥት በደቡብ ምሥራቅ ላሙ ደሴት በኩል ከሶማሊያ ጋር የሚያዋስነውን ድንበር በመዝጋት ወሰን ተሻጋሪ የንግድ ልውውጦችን አግዷል።

ባለፈው ሳምንት ማንዴራ በምትባለው የኬንያ ግዛት ውስጥ በአል ሸባብ ታጣቂዎች ተፈፀመ በተባለ ጥቃት አንድ የፖሊስ አባል ከተገደለ በኋላ የኬንያ ባለሥልጣናት በድንበር አካባቢ ያለውን ጥበቃ አጠናክረዋል።

ከቀናት በፊትም በሰሜናዊ ኬንያ የማንዴራ ግዛት ውስጥ የሽብር ጥቃት ሊፈፀም ይችላል በሚል የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቋረጥ ተደርጓል ሲል ቢቢሲ በድህረ-ገፁ አስነብቧል።

ካለው የደኅንነት ስጋት በመነሳት ከሳምንት በኋላ የኬንያ መንግሥት ከሶማሊያ ጋር በላሙ በኩል የሚያዋስነውን ድንበር ላልተወሰነ ጊዜ ለመዝጋት መወሰኑን አስታውቋል ።