የሱዳን ተቃዋሚዎችና ወታደራዊ ኃይሉ በኢትዮጵያ አደራዳሪነት በድጋሚ ለመነጋገር ተስማሙ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ልዩ መልእክተኛ በመሆን ካርቱም የሚገኙት አምባሳደር ሙሐመድ ድሪር ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ወታደሩ በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን የፖለቲካ እስረኞች ለመልቀቅ ተስማምቷል።

ተቃዋሚዎች አሁንም የሲቪል አስተዳደር እንዲመሰረት እየጠየቁ ነው።

በተቃዋሚዎችና በወታደሩ መካከል እየተደረገ የነበረው ውይይት የተቋረጠው በርካታ ተቃዋሚ ሰልፈኞች መገደላቸውን ተከትሎ ነበር።

 ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ተቃዋሚዎች በጠሩት ሕዝባዊ አመፅ በርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የስራ ማቆም አድማ ተመትቷል።

ሐኪሞች የተገደሉት 118 ሰዎች ናቸው ሲሉ የመንግሥት ባለስልጣናት ግን 61 ሰዎች ከልዩ ኃይሉ በተተኮሰ ጥይት መሞታቸውን ይናገራሉ።

ወታደሮች የካርቱምን አውራ ጎዳናዎች የሚጠብቁ ሲሆን በርካታ የንግድ ተቋማት ተዘግተዋል።

ማክሰኞ እለት ኢትዮጵያ አሸማጋይ ሆና በተቀመጠችበት ጠረጴዛ ሁለቱም ወገኖች የሲቪል አስተዳደር ለመመስረት ተስማምተዋል።

ተቃዋሚዎችም ከዛሬ ጀምሮ ዜጎች በሥራ ገበታቸው ላይ እንዲገኙም ጥሪ አቅርበዋል።

ሕዝባዊ አመፁን በቅድሚያ የጠራው የሱዳን የሙያ ማህበራት ዜጎች ወደ ሥራ ገበታቸው ይመለሱ የሚለውን ስምምነት ተቀብሎታል።

ወታደራዊ ኃይሉ በይፋ ውይይቱን ለመቀጠል መስማማት አለመስማማቱን አልተናገረም።

ነገር ግን የሽግግር መንግሥቱ አባል የሆኑት ሳላህ አብደልካሀልክ ለቢቢሲ ፕሮግራም እንደተናገሩት ከተቃዋሚዎች ጋር ስልጣንን እኩል ለመጋራት ስምምነት ላይ ሳይደረስ አልቀረም ብለዋል።

ቢሆንም ግን አሁንም የሽግግር መንግሥቱ ሊቀመንበር ከወታደሩ እንዲሆን እንደሚፈልጉ አልሸሸጉም።

ወታደራዊ ኃይሉ ፕሬዝዳንት ኦማር አል በሺርን ከስልጣን በማውረድ ላይ ቁልፍ ሚና የተጫወተ ሲሆን በርካታ የወታደሩ ሹማምንቶች አሁንም በእስር ቤት ይገኛሉ ሲሉ ተናግረዋል።

ነገር ግን የሽግግር መንግሥቱ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመደራደር ዝግጁ ነው ሲሉ አክለዋል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የአሜሪካ ልዑካን ቡድን ወደ ሱዳን እንደሚያቀናና ሁለቱ ወገኖች ንግግር እንዲጀምሩ ለማድረግ እንደሚጥር አስታውቆ ነበር።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሁለቱ ወገኖች ጉዳያቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይተው እንዲፈቱ ለማግባባት ወደ ሱዳን ማቅናታቸው ይታወሳል።

አንዳንድ ከሱዳን የሚወጡ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ 15 አባላት ያሉት የሽግግር ምክር ቤት እንዲቋቋምና ስምንት አባላቱ ከተቃዋሚዎች ሰባቱ ደግሞ ከወታደሩ እንዲሆን ሀሳብ ማቅረባቸው ይነገራል።/ቢቢሲ/