በሱዳን የተካሄደው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ከሸፈ

የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት በሀገሪቱ የተካሄደው መፈንቅለ መንግስት ሙከራ መክሽፉን አስታወቀ፡፡

የመፈንቅለ መንግስት መኩራ መካሄዱ የተሰማው የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት እና ተቃዋሚዎች ስልጣንን በመጋራት በሀገሪቱ ሲካሄድ የቆየውን ተቃውሞ ለማርገብ ጥረት እያደረጉ ባሉበት ወቅት ነው ተብሏል፡፡

ከከሸፈው መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጋር ተያይዞ 16 ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የምክር ቤቱ አባል ጄኔራል ጀማል ኦማር አስታውቀዋል፡፡

ጄኔራሉ የሀገሪቱ ጦር ወታደሮች፣ የብሄራዊ ደህንነነት አባላት፣ የፀጥታ አካላት እንዲሁም ባለስልጣናት በዚህ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተሳታፊ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የተወሰኑት ተሰናብተው የነበሩ ናቸው ብለዋል፡፡

መደበኛ የፀጥታ አካላት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራውን  ማክሸፋቸውን የገለጹት ጄኔራል ጀማል መፈንቅለ መንግስቱ መቼ እንደተካሄደ ግን ከመግለፅ ተቆጥበዋል፡፡

ይህ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤቱ እና በተቃዋሚዎች የተደረሰውን ስምምነት ለመቀልበስ ያለመም ነው ብለዋል፡፡

የፀጥታ አካላት በአሁኑ ወቅት ይህን የመፈንቅለ መንግስት መኩራ በማሴር ሲሳተፉ የነበሩ አካላትን በቁጥጥር ስር ለማዋል እየሰሩ ይገኛሉም ነው ያሉት።

የመፈንቅለ መንግስት ሙከራው በተሰማበት ወቅት የወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤቱ አባላትና የተቃዋሚ አመራሮች ባለፈው ሳምንት በደረሱት ስምምነት ዝርዝር ጉዳዮች ላይ በካርቱም ውይይት ላይ እንደነበሩ ተገልጿል። (ምንጭ፡- አልጀዚራ)