የግብፅ ፍርድ ቤት 14 የእስላሚክ ስቴት እጩ አባላትን በእስራት ቀጣ

የአሸባሪው የእስላሚክ ስቴት ዕጩ አባላት ለመሆን ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 14 ግለሰቦችን የግብፅ ፍርድ ቤት ከሶስት እስከ 25 አመታት በሚደርስ ፅኑ እስራት ቀጥቷል፡፡

ግለሰቦቹ በሶሪያ እና ኢራቅ የሚንቀሳቀሳውን አሸባሪው ቡድን እስላሚክ ስቴት ለመቀላቀል በመሞከራቸው ነው ለእስራት የተዳረጉት፡፡

በተጨማሪም ግለሰቦቹ እ.አ.አ ከ2016 እስከ 2018 ባሉት አመታት የመንግስት ተቋማትን በመሰባበር፤ በሃይል ስልጣንን ለመንጠቅ በተደረጉ ሙከራዎችና በሌሎችም የህግ ጥሰቶች ተጠያቂ መሆናቸውን ነው የሲጂቲኤን ዘገባ ያመለከተው፡፡

ህገወጥ የጦር መሳሪያዎችን ማከማቸትና አሸባሪ ቡድኑን መቀላቀል የሚሉ ክሶችም ቀርበውባቸዋል፡፡

ግብፅ እንደ አውሮፓውያኑ 2013 የቀድሞ ፕሬዚዳንቷ ሞሃመድ ሙርሲ በህዝባዊ አመፅ ስልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ እና የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ ከ2014 ጀምሮ መታገዱን ተከትሎ የተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶች ሰለባ መሆኗ ይታወሳል፡፡