የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ሕብረት በሱዳን ሰላማዊ ሽግግር እንዲደረግ ለተጫወቱት ሚና የምስጋና ፕሮግራም አዘጋጀ።
ሚኒስቴሩ በወታደራዊ ሽግግር ምክር ቤት እና በነጻነት እና ለውጥ ኃይሎች መካከል ሲደረግ የነበረው ድርድር የሽግግር ሕገመንግስት እና የፓለቲካ ስምምነት በመፈራረም መጠናቀቁን ተከትሎ ነው የምስጋና ፕሮግራሙን ያዘጋጀው።
በዚህም ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ሕብረት ሁለቱን ወገኖች በማደራደር ላበረከቱት አስተዋጽኦ እና ለተጫወቱት ቁልፍ ሚና በማመስገን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እና ዳይሬክተር ጄኔራሎች በተገኙበት ሽልማት አበርክቷል።
ሽልማቱ የተበረከተው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ፣ የሱዳን ልዩ ልዑክ አምባሳደር መሃሙድ ድሪር፣ በሱዳን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ እና የአፍሪካ ሕብረት ልዩ ልዑክ መሃመድ ሀሰን ላባት ነው ።
ሽልማቱን የወታደራዊ ሽግግር ምክር ቤት የፓለቲካ ጉዳዮች ተጠሪ ጄነራል ሸምሰዲን አል ካባሺ በተገኙበት ያበረከቱት ደግሞ የሱዳን ተጠባባቂ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ኦማር ዳሃብ ናቸው።
የሱዳን ተጠባባቂ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ኦማር ዳሃብ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ ኢትዮጵያና የአፍሪካ ሕብረት በሱዳን ሰላም እንዲሰፍንና የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት በአደራዳሪነት ለተጫወቱት ቁልፍ ሚና ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የምስጋና ሽልማቱ በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ያለውን ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ የሚያሸጋግርና በቀጣይ በሁለቱ አገራት መካከል የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር በተለያዩ የትብብር መስኮች ለሚከናውኑ ተግባራት መልካም መደላድል እንደሚፈጥር ይታመናል። (ምንጭ፡- በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ)