የሊቢያ ተዋጊዎች የኢድ በአልን በማስመልከት ጊዜያዊ የእርቅ ስምምነት አደረጉ

የሊቢያ ዋነኛ ተቀናቃኝ ተዋጊ ቡድኖች ለሶስት ቀናት የሚከበረው የኢድ አል አድሃ በዓልን በማስመልከት ጊዜያዊ ስምምነት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

ይህንንም ውሳኔ የተባበሩት መንግሥታት ይበል የሚያሰኝ ነው ብሎታል።

ቅዳሜ እለት ቤንጋዚ ላይ በደረሰ የቦምብ ጥቃት ሶስት ሰራተኞቹን ያጣው የተባበሩት መንግሥት ድርጅት በዚህ የሰላም ስምምነትም እንደ አንድ አደራዳሪ ሆኖ ቀርቧል።

በዚህ ስምምነት ላይ በሊቢያ መዲና ትሪፖሊ ከፍተኛ ጥቃትን ሲፈፅም የነበረው ወታደራዊ ኃይል ኃላፊ ጄኔራል ካሊፋ ሃፍተር ዋነኛ ተደራዳሪ ናቸው።

የአለም ጤና ድርጅት እንደዘገበው ከሚያዝያ ጀምሮ በነበረው ጥቃት አንድ ሺ ሰዎች ተገድለዋል።

"ጄኔራሉ ለእርቁ የተስማሙት ሊቢያውያን የኢድን በአል በሰላም እንዲያከብሩ ነው" በማለት ቃል አቀባያቸው አህመድ አል ሜስማሪ ገልጿል።

እርቁ ቅዳሜ ከ9 ሰአት የጀመረ ሲሆን፣ ሰኞ እስከ ከሰአትም እንደሚቀጥል ቃል አቀባዩ አክለው ተናግረዋል።

ኢድ አል አድሐ በመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ አምላክ ለአብርሃም በህልም ተገልፆ አንድ ልጁን እንዲሰዋ ትእዛዝ ካስተላለፈለት በኋላ፤ መስዋእቱን ለማድረግ በሚዘጋጅበት ወቅት በግ የላከበትን ቀን የሚታወስበት ነው።

በመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ 1 ሺህ 440ኛው ዓመተ ሒጅራ የኢድ አል አድሐ አረፋ በዓል በትላንትናው ዕለት ተከብሮ ውሏል፡፡ (ምንጭ፡-ቢቢሲ)