የተመድ ዋና ጸሐፊ እና ስምንት የአፍሪካ ሀገራት ርእሳነ መንግሥታት በሱዳን የለውጥ ስምምነት ላይ ይገኛሉ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጀት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ ስምንት የአፍሪካ ሀገራት ርእሳነ መንግሥታት፣ የአውሮፓ ኅብረት ፕሬዚዳንት እንዲሁም የአረብ እና የምዕራባውያን ሀገራት መሪዎች ቅዳሜ ዕለት በሱዳን በሚደረገው የፖለቲካ ለውጥ እና ሕገ-መንግሥት የማፅደቅ ስምምነት ላይ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የሱዳን የነፃነት እና የለውጥ ኃይሎች እና የወታደራዊ ሽግግር ምክር ቤት ታሪካዊ የተባለውን ስምምነት ለማድረግ መስማማታቸው ይታወሳል።

በስምምነት ፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ይገኛሉ ተብለው የሚጠበቁት የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር የሆኑት የግብጹ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ ኤል-ሲሲ፣ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ፣ የቻድ ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ እና የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ሞሳ ፋቂ ናቸው።

በዚህ ታሪካዊ ስምምነት ላይ የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካዮች፣ ስድስት ሀገራትን ያከተተው የገልፍ ኅብረት ምክር ቤት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና ሌሎች የባሕረ-ሰላጤ ሀገራት መሪዎች እንደሚገኙም ይጠበቃል።

ቅዳሜ ዕለት ለሚደረገው ሕገ-መንግሥት የማፅደቅ ስምምነት ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፤ ስምምነቱ የወታደራዊ ሽግግር ምክር ቤት ሊቀበንበር አብዴል ፋታህ አል-ቡርሃንን የመጀመሪያው የሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ያደርጋቸዋል ተብሏል።

(ምንጭ፦አልሸርቅ አል-አውሳጥ)