ሱዳን ለሦስት ዓመታት ለሚቆየው የሽግግር መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ሾመች

ሱዳን ለሦስት ዓመታት ለሚቆየው የሽግግር መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ሾመች።

አዲስ የተሾሙት ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሃምዶክ የሽግግር መንግሥቱ መሪ በመሆን ቃለ መሃላ የፈፀሙ ሲሆን፣ በቃለ መሃላቸው በአገሪቱ ያለውን ሰላም ማረጋገጥ እና ለምጣኔ ሐብታዊ ቀውሶች እልባት መስጠት ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ እንደሆነ ገልፀዋል።

ሌተናንት ጄነራል አብደል ፈታህ አብደልራህማን ቡርሃን ለሉዓላዊ ምክርቤቱ መሪ ሆነው መምራት ከጀመሩ በኋላ የተሾሙት ጠቅላይ ሚንስትሩ እስከ ቀጣዩ የአገሪቷ ምርጫ ድረስ እንደሚያስተዳድሩ ተገልጿል።

የሉዓላዊ ምክር ቤቱና ሃምዶክ በቃለ መሃላ ሥነስርዓቱ ላይ ሱዳን ኦማር አል በሽር ሥልጣን በኋላ ከወታደራዊ አገዛዝ ሥርዓት የተላቀቀችበት የመጀመሪያው ጊዜ ብለውታል።

ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በበኩላቸው አሁን የተመሰረተው መንግሥት በአገሪቷ የነበረውን የወታደራዊ አገዛዝ ሥርዓት እንዲያከትም ያደርገዋል በማለት ተስፋ ሰንቀዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ሃምዶክ ከአውሮፓዊያኑ 2011 ጀምሮ በተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የምጣኔ ሐብት ባለሙያ ሆነው አገልግለዋል።

መንግሥት ቅድሚያ ሰጥቶ ከሚሰራቸው ተግባራት መካከል፤ ጦርነትን ማስቆም፣ ዘላቂነት ያለው ሰላም መገንባት፣ የምጣኔ ሐብት ቀውስን መፍታት እና ሚዛናዊነቱን የጠበቀ የውጭ ፖሊሲ መገንባት እንደሆኑ ሃምዶክ ለሮይተርስ ዜና ወኪል አስታውቀዋል።

ባለፈው ዓመት ሃምዶክ የአገሪቷ የገንዘብ ሚኒስቴር እንዲሆኑ ከሥልጣን በተወገዱት ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር የታጩ ሲሆን ጥያቄው ሳይቀበሉት መቅረታቸውን ኤ ኤፍ ፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

በሱዳን የተፈጠረው ቀውስ የጀመረው ባለፈው ዓመት መጨረሻ አካባቢ ሲሆን አገሪቷን ለ30 ዓመታት ያስተዳደሩት ኦማር አል በሽር ከሥልጣን እንዲወርዱ በመጠየቅ ነበር።

የሲቪል መንግሥት እንሻለን የሚሉ የአገሪቷ ዜጎች ለወራት ተቃውሟቸውን ያሰሙ ሲሆን በእነዚህ ጊዜያትም የበርካቶች ሕይወት ማለፉ ይታወሳል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።