የቀድሞው የደቡብ ሱዳን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሪክ ማቻር ከፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ጋር ሊወያዩ ነው

የቀድሞው የደቡብ ሱዳን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሪክ ማቻር ከፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ጋር ሊወያዩ ነው።

ማቻር ከሳልቫ ኪር ጋር ለሚያደርጉት ውይይት ዛሬ ጁባ የገቡ ሲሆን፣ ለሁለት ቀናት በሚኖራቸው ቆይታም ሳልቫ ኪርን ጨምሮ ከሌሎች ተቀናቃኝ ሃይሎች ጋር በተደረሰው የሰላም ስምምነት ተፈጻሚነት ዙሪያ እንደሚወያዩ ተገልጿል፡፡

የአሁኑ የማቻር ጉብኝት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ለሚደረገው ጥረት ተስፋን ሰጪ ነው የሚል እምነት ተጥሎበታል።

በፈረንጆቹ 2011 ከሱዳን ተነጥላ ሉዓላዊ ሀገር የሆነችው ደቡብ ሱዳን ሁለት አመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ወደ እርስ በርስ ግጭት ገብታ ሰላም ከራቃት ሰንብታለች።

በወቅቱ ለተፈጠረው ግጭት ሳልቫ ኪር ሪክ ማቻርን ከስልጣን ማንሳታቸው መሆኑም ይነገራል።

ይህን ተከትሎ የተፈጠረውን ቀውስ እልባት ለመስጠት ከአንድ አመት በፊት የሰላም ስምምነት ቢደረስም እስካሁን ተፈጻሚ ሳይሆን ቆይቷል።

ለዚህ ደግሞ ሳልቫ ኪር ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታትና ሂደቱን ተፈጻሚ ለማድረግ የገንዘብ አቅም የለኝም የሚል ምክንያት ያቀርባሉ ነው የተባለው፡፡ (ምንጭ፡-ሬውተርስ)