አሜሪካ ከ30 ዓመት በኋላ በሶማሊያ ኤምባሲዋን ከፈተች

አሜሪካ ከሶማሊያ የርስ በርስ ጦርነት ጋር በተያያዘ ዘግታው የነበረውን ኤምባሲዋን ከ30 ዓመት በኋላ ከፈተች።

ሶማሊያን ለረዥም ጊዜ አስተዳድረዋት የነበሩት ዚያድ ባሬ በጎርጎሳውያኑ 1991 ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ የተለያዩ የጎሳ መሪዎች እርስ በእርሳቸው ሲዋጉ ቆይተዋል።

ሶማሊያ ከዚህ በኋላ በጎሳ የጎበዝ አለቆች እና በእስላማዊ ቡድን ወታደሮች በሚደረጉ ውጊያዎች ስትታመስ ቆይታለች።

ረቡዕ ዕለት ከአሜሪካ ኤምባሲ የወጣ መግለጫ እንደሚያስረዳው አሜሪካ ኢምባሲዋን በሞቃዲሾ ለመክፈት የቻለችው ባለፈው አመት ቋሚ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በሞቃዲሾ እንዲኖራት ማድረጓን ተከትሎ መሆኑ ተገልጿል።

አክሎም "ይህ መደበኛ የሆነውን የአሜሪካና የሶማሊያ ግንኙነትን ዳግም ማስቀጠል፣ የአሜሪካና ሶማሊያ ግንኙነት መጠናከሩንን ማሳያ፣ እንዲሁም የመረጋጋቷ፣ የዕድገቷ፣ እንዲሁም የሶማሊያና የአካባቢው ሰላም መሻሻሉን ማሳያ ነው" ይላል።

በሶማሊያ የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ያማማቶ የኤምባሲውን መከፈት "ወሳኝና ታሪካዊ" ያሉ ሲሆን፣ ዓላማውም "በሶማሊያ በ2013 ለተቋቋመው የፌደራል መንግሥት እውቅና በመስጠት አሜሪካ በሞቃዲሾ ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ተሳትፎ መደበኛ ማድረግ" መሆኑን ገልፀዋል።

እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ አሜሪካ የሶማሊያ ዋነኛ አጋር ስትሆን ባለፈው ዓመት ብቻ 730 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አድርጋለች። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)