በሩዋንዳ ታዋቂ የጎብኚዎች መናኸሪያ በተፈፀመ ጥቃት 14 ሰዎች ሞቱ

በሩዋንዳ ታዋቂ የጎብኚዎች መናኸሪያ በተፈፀመ ጥቃት 14 ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል፡፡

ጥቃቱ መፈጸሙን ተከትሎ የሩዋንዳ ፖሊስ በወሰደው አፀፋዊ ምላሽ ከጥቃት አድራሾቹ መካከል 19ኙ መገደላቸውንና ሌሎች ማምለጣቸውን አስታውቋል፡፡

የሩዋንዳ ፖሊስ ቃል አቀባል ጆን ቦስኮ በኮንጎ ጠረፍ አካባቢ በሚገኘው የመዝናኛ ስፍራ ባለፈው አርብ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ ሌሎች 5 ግለሰቦች ታስረው ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የእሳተ ገሞራ ብሄራዊ ፓርክ የሚገኝበት ይህ አካባቢ በበርካታ ቱሪስቶች የሚጎበኝ ስፍራ ነው፡፡

በተለይም በሩዋንዳ ብቻ የሚገኙትን ጎሬላዎች ለመመልከት በርካታ ጎብኚዎች ወደስፍራው እንደሚያቀኑ የሲጂቲኤን ዘገባ አመልክቷል፡፡

እስካሁን በቱሪስቶች ላይ ስለደረሰው ዝርዝር ጉዳት ዘገባው ባያመለክትም በጥቃቱ 18 ሩዋንዳውያን መቁሰላቸው ተነግሯል፡፡

ባለፉት ጊዜያት በማዕድን ሃብት በበለፀገችው ምስራቃዊ ኮንጎ እና በሩዋንዳ አዋሳኝ ቀጠና በርካታ ታጣቂ ቡድኖች ጥቃቶችን በመሰንዘር ላይ ይገኛሉ፡፡

የሩዋንዳ ቱሪዝም እንቅስቃሴዎችን የሚደግፈው የሩዋንዳ ልማት ቦርድ በሰጠው መግለጫ ችግሩ በአሁኑ ወቅት በቁጥጥር ስር መዋሉን ነው የገለፀው፡፡