መንግስት ሰልፈኞች ሁከትና ብጥብጥ እንዲያባብሱ እንደማይፈቅድ የግብጹ ጠቅላይ ሚኒስትር  አስጠነቀቁ

መንግስት ሰልፈኞች ሁከትና ብጥብጥ እንዲያባብሱ እንደማይፈቅድ የግብጹ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ ማድቡሊ አስጠንቅቀዋል፡፡

መናሻውን ሰሜን አፍሪካዊቷን  ቱኒዚያ ያደረገው የአረቡ አለም የፀደይ አቢዮት ከስምንት አመታ በፊት ነበር ግብፅን የመታው፡፡

ህዝባዊ አመፁ ወታደራዊ ስርዓትን ገርስሶ በፈርኦኖች ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሲቪል አስተዳዳር ተክሎም ነበር፡፡ ምንም እንኳን እድሜ ባይኖረውም ቅሉ፡፡ ይህ አቢዮት ግዜ ጠብቆ  ያገረሸ ይመስላል፡፡

ባለፈው ወር በግብጹ በፕሬዚዳንት አብድል ፋታህ አል ሲሲ ላይ የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞም አሁንም ድረስ እንደቀጠለ ነው፡፡

ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ እ.አ.አ በ2016 ይፋ ያደረጉት የግብጽ የኢኮኖሚ ሪፎርም ተግባራዊ ባለመሆኑና የሀገሬው ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው የኢኮኖሚ ጫና መበርታቱን ተከትሎ ህዝባዊ ተቃውሞዎቹ ተበራክተዋል፡፡ ተቃውሞዎቹም ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ከስልጣን እንዲወርዱ የሚጠይቁ ናቸው፡፡

የግብጹ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ ማድቡሊ መንግስታቸው ሰልፈኞች ብጥብጥ እንዲያሰራጩ አይፈቅድም ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቃውሞው በሀገሪቱ ግራ መጋባትን ለመፍጠር የተነደፈ የውጭ ሀይሎች እጅ ያለበትና ጭካኔ የተሞላው የጦርነት አካል ነው ሲሉ አውግዘውታል፡፡

ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ መጠነ ሰፊ ተቃውሞዎች አደጋቸው የበዛ ነው ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስጠንቅቀዋል፡፡

እ.አ.አ በ2011 አምባገነኑን መሪ ሆስኒ ሙባረክን ከስልጣን ለማውረድ በሀገሪቱ ተከስቶ የነበረውን ህዝባዊ አመጽ በማስታወስ የግብጽ ህዝብ መሰል ብጥብጥና ሁከት ዳግም እንዲደገም አይፈቅድም ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በግብጽ በተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ እስካሁን አክቲቪስቶችን ጨምሮ 3000 ሰዎች መታሰራቸውን መረጃዎች አመላክተዋል፡፡   

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን እስካሁን የተወሰዱ እርምጃዎች ህግን መሰረት ያደረጉ ናቸው ብለዋል፡፡

ቀውሱን ተከትከሎ ምንም አይነት የከፋ ችግር አላስተናገድንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህም የሀገሪቱን የፖሊስ አባላት አመስግነዋል፡፡

ኢኮኖሚያዊ ጫናው በግብጻውያን ላይ እያሳደረ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ያመኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገር መገንባት ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ ሂደት ነው ማለታቸውን ሜይል ኦንላይን ዘግቧል፡፡