ደቡብ ሱዳን የኢቦላ ቫይረስ መከላከያ ክትባት ልትሰጥ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት ገለጸ

ደቡብ ሱዳን የኢቦላ ቫይረስ መከላከያ ክትባት ልትሰጥ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት ገለጸ፡፡

ሀገሪቱ ክትባቱን የምትሠጠው በሽታው በኮንጎ አገርሽቶ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት የደቡብ ሱዳን ጎረቤት በሆነችው ኮንጎ የተነሳው የኢቦላ ቫይረስ ወደ ሀገሪቷ እንዳይዛመት እና ሃገሪቷን አደጋ ላይ እንዳይጥላት ስጋት መኖሩን ገልጿል፡፡

በመሆኑም ድርጅቱ በቅርብ ቀናት ውስጥ በሃገሪቱ ፀረ-ኢቦላ ክትባት ለመሥጠት መዘጋጀቱን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

ተቋሙ ባወጣው መግለጫ መሠረት የደቡብ ሱዳን የጤና ሚኒስቴር ከስምንት ቀናት በኋላ በመዲናዋ ጁባ የሚገኙ የጤና ሠራተኞች እና ሌሎች ለቫይረሱ ተጋላጭ ሊሆኑ የሚችሉ አካላት ይከተባሉ ተብሏል፡፡

በአጠቃላይ 4ሺህ ሰዎችን ለመከተብ ያቀደችው ደቡብ ሱዳን የዓለም የጤና ድርጅት ለ2ሺ ዜጎቿ የክትባት ቁሳቁስ እንደሚያቀርብላት ገልጿል፡፡

በታሪክ ሁለተኛው ገዳይ በሽታ መሆኑ የተገለጸው ይህ በሽታ እስከ አሁን ወደ ኮንጎ ጎረቤት ሃገራት ባይዛመትም ክትባቱ ግን በኡጋንዳም መጀመሩን ዘገባው አስነብቧል፡፡

በኮንጎ እስካሁን 446 ሰዎች በኢቦላ እንደተጠቁ እና 235 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው እንዳለፈ የሃገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል፡፡

በቫይረሱ ከተጠቃ አንድ ሰው ከዚያም ከሰው ወደ ሰው በንክኪና በተለያዩ መንገዶች እንደሚተላለፍ በጥናት የተረጋገጠው የኢቦላ ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ የታወቀው እኤአ በ1976 በሱዳን እና በቀድሞዋ ዛየር በአሁኗ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ (ምንጭ፡-አሶሺየትድ ፕረስ)