ግብጽ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ ጥብቅ ሕግ አወጣች

ግብጽ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚለቀቁ የሃሰት ዜናዎች እና ለሽብር ስራ የሚያገለግሉ ድረ ገጾች ላይ እስከ መዝጋት የሚደርስ ጠበቅ ያለ አዲስ ህግ አውጥታለች።

አዲሱ ህግ በማህበራዊ ሚዲያ እና በድረገጽ ተጠቃሚዎች በተለይ ከ5 ሺህ በላይ ተከታይ ያላቸው ሰዎች የሚያስተላልፉት መረጃ የብሔራዊ ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥል ከሆነ ከመዝጋት ባለፈ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የ14 ሺህ ዶላር ቅጣት ሊያስጥል የሚያስችል ህግ ነው ተብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ የግብጽ የደህንነት መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ የሃገሪቱ ሚኒስትሮች በየትኛውም ሚዲያ ላይ አንዳይወጡ የሚል ማስጠንቀቂያ አውጥቷል።

ማስጠንቀቂያው ሚዲያ ጣቢያዎችንም የሚመለከት ሲሆን ከሚኒስትሮች ጋር ማንኛውንም አይነት በስልክ፣ በቀጥታም ይሁን በመደበኛ ዝግጅቶች ላይ እንዳይገቡ የሚያግድ ነው ተብሏል።

ማስጠንቀቂያው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹ ቃል አቀባዮችን የማያጠቃልል ሲሆን፣ ለምን እንደወጣ እና እስከመቼ እንደሚቆይ የደህንነት መስሪያ ቤቱ ያለው ነገር የለም። (ምንጭ፡-አልጀዚራ)