ኬንያዊው ለጋስ መምህር የ1 ሚሊየን ዶላር አሸናፊ ሆኑ

80 በመቶ ደሞዛቸውን በድህነት ውስጥ ለሚገኙ የሚለግሱት ኬኒያዊው መምህር የ1 ሚለየን ዶላር ዓለም አቀፍ ሽልማት አሸናፊ ሆኑ።

የሂሳብና የፊዚክስ መምህር የሆኑት ፒተር ታባቺ በኬንያ ገጠራማ አካባቢ ነው የሚያስተምሩት።

ከሚያስተምሯቸው ተማሪዎች መካከልም አብዛኛዎቹ በድህነት ውስጥ የሚገኙ ሲሆኑ፥ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት በአንድ ወላጅ የሚያድጉ ወይንም ወላጅ አልባ ናቸው።

መምህር ታባቺ ታዲያ ትምህርት ቤቷ ባለት አንድ ኮምፒዩተር ተጠቅመው እንዲሁም ወደ ኢንተርኔት ካፌዎች ውስጥ ገብተው የቃረሙትን ለተማሪዎቻቸው ያስተላልፋሉ።

በትምህርት ቤቱ ውስጥ እርሳቸው በሚመሩት የሳይንስ ክበብ ውስጥ ተማሪዎቻቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አስችለዋል።

የሂሳባዊ ሳይንስ ቡድናቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ በአሜሪካ አሪዞና ግዛት በሚካሄደው ዓለምአቀፍ የሳይንስና የኢንጅነሪንግ ውድድር አልፏል።

በተጨማሪም የመምህሩ ተማሪዎች በአካባቢያቸው የሚገኝ ተክልን በመጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያመነጭ የሚያስችል ፈጠራ በመስራታቸው ከሮያል ሶሳይቲ ኦፍ ኬሚስተሪ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ተማሪዎቹ የሚያጋጥማቸውን ችግር አለሁላችሁ በማለት ካላቸው አብዛኛውን የሰጡት ኬንያዊው መምህር ሽልማታቸውን የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በመሄድ ተቀብለዋል።

መምህሩ ሽልማቱን በተቀበሉበት ወቅት አፍሪካ በየዕለቱ አዳዲስ ምዕራፎችን እየጀመረች እንደምትገኝ ጠቅሰው፥ የዛሬው አንደኛው ነው ብለዋል።

ሽልማቱ እሳቸውን ታዋቂ ከማድረግ ይልቅ በአህጉሪቱ ያለውን ወጣት ትውልድ እምቅ አቅም የሚያስተዋውቅ መሆኑን አንስተዋል።

(ምንጭ፦ ኤፍቢሲ )