የሊቢያ ግጭት መባባሱ ሰብዓዊ እርዳታን ለማድረስ አዳጋች እያደረገው ነው ተባለ

የሊቢያ ግጭት መባባሱ ለዜጎች የሰብዓዊ እርዳታን ለማድረስ አዳጋች እያደረገ መሆኑ ተገለጸ፡፡

በሊቢያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እውቅና በተሰጠው መንግስትና በከሊፋ ሀፍጣር በሚመራው የሊቢያ ብሄራዊ ጦር መካከል ከሶስት ሳምንታት በፊት የተጀመረው ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡

የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው በግጭቱ እስካሁን 254 ሰዎች ሲሞቱ 1ሺህ 228 ሰዎች ቆስለዋል፤ 32 ሺህ ሰዎች ደግሞ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ቀናት ብቻ 34 ሰዎች መሞታቸውንም ነው ድርጅቱ ያስታወቀው፡፡

በሊቢያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረዳት መልዕክተኛ ማሪያ ዶ ቫሌ ሪቤይሮ በሁለቱ ወገኖች መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት መባባሱ የተረጂዎችን ቁጥር ወደ 21 ሺህ አድርሶታል ብለዋል፡፡ ሰብዓዊ እርዳታ የማድረሱን ስራም አስቸጋሪ እንዳደረገው ነው የተገለፀው፡፡

የተመድ ድጋፍ ያለውንና የሊቢያ ብሄራዊ አንድነት መንግስት ተብሎ የሚጠራውን ኃይል በጠመንጃ ለማስወገድ በከሊፋ ሀፍጣር የሚመራው የሊቢያ ብሄራዊ ጦር እያደረገው ያለው ውጊያ ወደፊትም ሊቀጥል እንደሚችል ልዩ መልዕክተኛዋ አሳስበዋል፡፡

እስከ መጪው ግንቦት ወር ተጨማሪ የ10 ነጥብ 2 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ካልተገኘ በሊቢያ ሰብዓዊ ቀውሱ ሊባባስ እንደሚችል ነው የተገለጸው፡፡

(ምንጭ፡-አልጀዚራ )