ለአፍሪካ ወጣቶች የሥራ እና የክህሎት ችግሮች ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት ይገባል – ሙሳ ፋቂ ማሀመት

አፍሪካን የተሻለች አህጉር ለማድረግ የወጣቶችን የሥራ እና የክህሎት ችግሮችን ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማሀመት ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ ሁለት አመታት ቢያንስ የአንድ ሚሊየን ወጣቶችን ህይወት ያሻሻላል የተባለውን መርሃ ግብር ይፋ ያደረጉት ሊቀመንበሩ ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ምቹ የሆኑ ፖሊሲዎች መቀረፅ እንደሚገባቸውም አመልክተዋል፡፡

ሊቀመንበሩ በፎረሙ ላይ ለተሳተፉት ወጣቶች በኔልሰን ማንዴላ ቤት ነው የተሰበሰባችሁት በማለት አነቃቅተዋቸዋል፡፡ ያላችሁን እድል ሁሉ ወደ ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት መቀየር ይገባችኋል ሲሉም አክለዋል፡፡

የአፍሪካ ወጣቶች ትኩረት እንደተነፈጋቸውና በቀጣይ የሚሰሩ ፖሊሲዎች የወጣቶችን ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጡት እንደሚደረግም አክለው ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ ሕብረት የወጣቶች መልዕክተኛ አያ ቼዲ በበኩላቸው አህጉሩን ሰላማዊ በማድረግ ያለውን የወጣቶች ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባ ተናገረዋል፡፡

አፍሪካ ወጣቶች በየትኛውም አህጉር በህጋዊ መልኩ ተንቀሳቅሰው በመስራት ህይወታቸውን መቀየር ይፈልጋሉ፤ ለዚህም መሰራት አለበት ብሏል፡፡ አካል ጉዳተኞችም ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ሲል አከሏል፡፡  

በፎረሙ ላይ የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በንግድ ሥራ የሚሳተፉ ወጣቶችን መርዳት፣ በትምህርት እንዲሁም ፖለቲካዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የአፍሪካ ወጣቶችን ተሳታፊ ማድረግ የሚሉት የጉባኤው የትኩረት አጀንዳዎች ነበሩ፡፡