ሶማሊያ ብሔራዊ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል ልታቋቁም ነው

ሶማሊያ የመጀመሪያውን ብሔራዊ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል ልታቋቁም ነው፡፡

ማዕከሉ በውስጣቸው የቴክኖሎጂ ቁሳቁሶችን የያዙ ፓርኮች፣ የፈጠራ ማዕከሎች፣ የመስሪያ ቦታዎች እና በዝቅተኛ ክፍያ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ኔትዎርክ አገልግሎቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ማዕከላትን ያካትታል ተብሏል፡፡
ግንባታው በሱማሊያ የቴሌኮም ቴክኖሎጂ እና ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ በሀገሪቱ ማዕከል ያደረገ ስነ ምህዳርን ለመፍጠር እና በሱማሊያውያን ፈጠራ ለሚመረቱ  ዲጂታል ምርቶች የገበያ ቦታ ለምፍጠር ያለመ ነው ተብሏል፡፡

የሀገሪቱ  የቀድሞ ቴሌኮም ኦፕሬተር አብዲ አሹር ሃሰን ስለግንባታው ሲናገሩ ግንባታው ከተጠናቀቀ እና አስፈላጊ ቁሳቁሶች ከተሟሉ በኋላ የፈጠራ ስራ አቅም ያላቸውን ወጣቶች በማዕከሉ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለመፍጠር እና በድረገፅ ገበያው ላይ እንዲሸጡ በማስቻል ጥሩ ገቢ የሚያገኙበት ሁኔታን ለመፍጥር ይረዳል ብለዋል፡፡

መንግስት በሁሉም የፌዴራል ከተሞች ውስጥ የፈጠራ ማዕከላትን ለማቋቋም ቁርጠኛ መሆኑን የሶማሊያ ቴሌኮም ቴክኖሎጂ ሚኒሰቴር አስታውቋል፡፡

በነዚህ ማዕከላት ግንባታም የሀገሪቱን ዜጎችን  ወደ መረጃ ማህበረሰብ  ለመለወጥ እና ዜጎችን ለዲጂታል ኢኮኖሚ ለማዘጋጀት ይረዳል ተብሏል፡፡

ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ የህግ እና የፖሊሲ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ላይ አተኩሮ ሲሰራ ቆይቷል ተብሏል፡፡  

አሁን ደግሞ ሕጎችና ፖሊሲዎች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መሆናቸው ከተረጋገጠ በኋላ ለወጣቱ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል በከፍተኛ የፉክክር መንፈስ የሚሰሩ በርካታ የፈጠራ ስራዎች እንደሚኖሩ ተስፋ ተደርጓል፡፡

የፕሮጀክቱ ሀሳብ ተግባረዊ ሲሆን በሶማሊያ ያለውን ውስን የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት፣ በጤናው፣ በግብርናው እና በንግዱ ዘርፍ ላይ ትልቅ ለውጥን በመፍጠር ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ የጎላ ሚና እንደሚጫወትም ይጠበቃል ተብሏል፡፡

የማዕከላቱ ግንባታ በውስጣቸው  በበቂ የቴክኖሎጂ ቁሳቁሶች የተሟሉ ፓርኮች፣ የፈጠራ ማዕከሎች፣ የመስሪያ ቦታዎች፣ ዝቅተኛ ክፍያ ያለው ኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ኔትዎርክ አገልግሎቶችና ዲጂታል የሆኑ የፈጣራ ስራዎችን  ለመደገፍ የሚያስችሉ የተለያዩ ድጋፎችን የያዙ ይሆናሉም ተብለዋል ፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሁሉም  የመንግስት ተቋማት እና  የግሉ  ዘርፍ ይህን የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል ግንባታን እውን ለማድርግ በጋራ እነዲሰሩ ጥሪ ማቅረቡን ዳልሰን ራዲዮ ዘግቧል፡፡