በሊቢያው ግጭት ከ42 ሺህ በላይ ሰዎች እንደተፈናቀሉ ተገለጸ

በሊቢያ መንግስት ወታደሮችና በጄኔራል ካሊፋ ኻፍታር ታማኝ ጦር መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት እስካሁን 350 ያህል ሰዎች ሲሞቱ ከ1 ሺህ 650 በላይ መቁሰላቸውና ከ42 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ተገለጸ፡፡

በደቡባዊ ትሪፓሊ በግጭት ቀጠና በእስር ላይ ያሉ ስደተኞችን ጨምሮ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም ህይወታቸው በአስጊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝና ከነዚህ ሰዎች መካከልም አብዛኞቹ ሴቶችና ህፃናት እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

ተፋላሚዎቹ ሰብዓዊ መብት ህግና ድንጋጌዎች በማክበር በአካባቢው የሚገኙ ሰዎችን ሰብዓዊ መብት በማክበር ግጭት እንዲያቆሙ ጥሪ የተደረገ ቢሆንም አሁንም በከባድ የጦር መሳሪያዎች፣ ሮኬቶችና በጦር አውሮፕላን የታገዘ ጦርነት እያካሄዱ እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡

ቀደም ሲል የመንግስታቱ ድርጅት ከሌሎች ሰብአዊ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በእስር ላይ የነበሩ እስረኞችን ጨምሮ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከግጭት ቀጠናው ማስወጣቱን ታውቋል፡፡

አሁንም በዚሁ አካባቢ በእስር ላይ የሚገኙ ስደተኞችና ነዋሪዎችን ከአካባቢው በማስወጣት የደህንነት ስጋታቸውን ለመቀነስ ወደ ሌሎች ቦታዎች በአፋጣኝ መዛዎር እንዳለባቸው ነው የተገጸው፡፡

(ምንጭ፡- ሲጂ ቲ ኤን)