ቱኒዚያ አቅራቢያ ስደተኞችን ያሳፈረች መርከብ ተገልብጣ 65 ሰዎች ሞቱ

በሜዲትራኒያን ባሕር ላይ ስደተኞች አሳፍራ ትጓዝ የነበረች መርከብ ተገልብጣ 65 ስደተኞች መሞታቸውን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት አስታወቀ።

ድርጅቱ እንዳለው፤ 16 ሰዎች ከአደጋው ተርፈዋል፡፡ ከአደጋው የተረፉት ስደተኞች እንደተናገሩት፤ መርከቧ ሐሙስ እለት ከሊቢያዋ ዙዋራ የተነሳች ሲሆን ከባድ ማዕበል አጋጥሟት ተገልብጣለች ብለዋል።

በፈረንጆቹ 2019 164 ስደተኞች ከሊቢያ ወደ አውሮፓ ሲያቋርጡ ሕይወታቸውን ማጣታቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ መረጃ ያሳያል።

በዚህ ዓመት ስደተኞችን አሳፍረው ወደ አውሮፓ ሲያቋርጡ ከደረሱ የመርከብ መገልበጦች ሁሉ ይህ የከፋው ነውም ተብሏል።

ከአደጋው የተረፉት በቱኒዚያ ባህር ኃይል ወደ ባህር ዳርቻው የሄዱ ሲሆን ወደ ቱኒዚያ ለመግባት ፍቃድ እስኪያገኙ እየጠበቁ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ከተረፉት መካከል አንድ ግለሰብ ለሕክምና ክትትል ወደ ሆስፒታል መላኩን የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ በመግለጫው ላይ አመልክቷል።

የቱኒዚያ ባህር ኃይል አደጋውን እንደሰማ ወደ ስፍራው ማቅናቱን የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር የተናገረ ሲሆን፣ በአደጋው ስፍራ ሲደርሱም የአሳ አጥማጆች መርከብ የተረፉትን ሲታደጉ ማግኘታቸውን በመግለጫቸው ላይ አሳውቀዋል።

ስደተኞቹ በአጠቃላይ ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገራት ዜጎች መሆናቸውም ታውቋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ተወካይ የሆኑት ቪንሰንት ኮቼቴል "ይህ አሳዛኝ እና ሰቅጣጭ አደጋ ዛሬም የሜዴትራኒያንን ባህር ለማቋረጥ በሚሞክሩ ስደተኞች ላይ እየደረሰ ነው" ብለዋል።

አንዳንድ መረጃዎች በመርከቧ ላይ ተሳፍረው የነበሩ ሰዎች ቁጥርን ከፍ እያደረጉ ስለሆነ የሟቾች ቁጥር ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል።

በርካታ ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚፈልጉ አፍሪካውያን ስደተኞች የሜዲትራኒያንን ባህር የሚያቋርጡ ሲሆን መነሻቸውም ሊቢያ ነች።

ስደተኞቹን የሚያጓጉዙ መርከቦች አሮጌ ሲሆኑ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች በአንድ ጊዜ ስለሚጭኑ ለመገልበጥ አደጋ የተጋለጡ ናቸው።

በ2019 ብቻ 15ሺህ 900 ስደተኞች አደገኛውን ባህር አቋርጠው አውሮፓ መግባታቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት አስታውቋል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)