ቡርኪናፋሶ ቤተ ክርስቲያን በደረሰ ጥቃት ስድስት ምዕመናን ተገደሉ

ትናንት በሰሜናዊ ቡርኪናፋሶ አምልኮ ላይ የነበሩ ክርስቲያኖች ላይ ተኩስ ተከፍቶ የቤተክርስቲያኒቱን ቄስ ጨምሮ ስድስት ምዕመናን መገደላቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት አስታወቁ።

ምዕመናኑ የካቶሊክ ቤተክርስትያን አባላት ሲሆኑ የጠዋት አምልኮ ስርዓት ላይ ነበሩ ተብሏል።

ጥቃቱ የደረሰባት ዳብሎ ከተማ ከንቲባ ኦስማኔ ዞንጎ የታጠቁ አካላት ወደ ቤተክርስቲያኒቱ ዘለው በመግባት ለማምለጥ በሚሞክሩት ላይ መተኮስ መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

ጥቃቱን ያደረሱት አካላት 20 እና 30 ይሆናሉ የተባለ ሲሆን ቤተ ክርስቲያኑንም አቃጥለዋል።

የከተማው ከንቲባ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል እንደገለፁት ሌሎች ሕንፃዎች ሲቃጠሉና ጤና ጣቢያው ላይ ዘረፋ ሲፈፀም መደናገጥ እነደተፈጠረና ጥቃቱ ከደረሰ በኋላ የከተማው ነዋሪዎች በፍርሃት ተውጠው ከቤታቸው ሳይወጡ ውለዋል ብለዋል።

የደህንነት ምንጮች ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል እንዳረጋገጡት ለከተማዋ ተጨማሪ ወታደራዊ ኃይል አቅራቢያ ከሚገኝ ከተማ ተልኳል።

በአካባቢው የሚኖር ጋዜጠኛ ለቢቢሲ እንደተናገረው ጥቃቱ የተፈፀመባቸው ክርስቲያኖች በከተማቸው የሚገኘው የወታደሮች ኃይል ወዲያውኑ ስላልደረሰላቸው ተበሳጭተዋል።

በቡርኪናፋሶ ጂሃዲስቶች በአምስት ሳምንት ውስጥ ጥቃት ሲፈፅሙ ይህ ሶስተኛቸው ነው ተብሏል፡፡

(ምንጭ፡-ቢቢሲ)