በደቡብ ሱዳን የምሽት ክለቦች መታገዳቸው ተገለጸ

በደቡብ ሱዳን መዲና ጁባ የሚገኙ የምሽት ክለቦች ሙሉ በሙሉ መታገዳቸውንና መጠጥ ቤቶች ላይ የሰአት እላፊ መጣሉን ቃል አቀባዩ ሜጀር ጀነራል ዳንኤል ጀስቲን አስታውቀዋል።

"የምሽት ክለቦች ሙሉ በሙሉ እንዲዘጉ የተላለፈው ውሳኔ ተግባራዊ እየሆነ ነው፤ የከተማው ነዋሪዎች ለከተማው ምክር ቤት የምሽት ክለቦች እየረበሿቸው እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲያማርሩ ነበር" ብለዋል ቃልአቀባዩ።

የጁባ አስተዳዳሪ አውግስቲኖ ጃዳላ ዋኒ በበኩላቸው ከሳምንት በፊት በፌስቡክ ባስተላለፉት መልዕክት "ያልተገቡ" ተግባራትን ለመከላከል የምሽት ክለቦች እንዲዘጉና በመጠጥ ቤቶችም የሰአት እላፊ አዋጅ እንዲተላለፍ መወሰኑን አሳውቀው ነበር።

በሰአት እላፊው አዋጅ መሰረት መጠጥ ቤቶች የሚሰሩበት ሰአት ከቀኑ ስምንት ሰአት እስከ ምሽቱ 1 ሰአት ድረስ ብቻ እንደሆነ ሱዳን ትሪቢውን ዘግቧል።

ከዚህም በተጨማሪ በሆቴል መቆየት የሚፈልጉ ጥንዶች ባለትዳር መሆን የሚጠበቅባቸው ሲሆን የጋብቻ ማስረጃ ሰርቲፊኬትም ሊያሳዩ እንደሚገባም ተደንግጓል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)