በሶማሊያ ለተከሰተው ድርቅ አስቸኳይ መፍትሄ ለማምጣት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥሪ አቀረበ

በሶማሊያ በተከሰተው ድርቅ እየደረሰ ላለው የሰባዊ ቀውስ አስቸኳይ መፍትሄ ለማምጣት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥሪ አቀረበ፡፡

በሶማሊያ በድርቅ ሳቢያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ለረሀብ እንደተዳረጉ የተመድ ሪፖርት አመላክቷል፡፡

ሶማሊያ በተደጋጋሚ ከሚደርስባት የሽብር ጥቃት ባለፈ አሁን ያጋጠማት የድርቅ አደጋ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባታል፡፡

ይህ የድርቅ አደጋ ደግሞ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሶማሊያዊያንን ለከፋ ርሀብ  እንደዳረገ ነው የተመድ ሪፖርት የሚያመለክተው፡፡

በሶማሊያ የተፈጠረው የዝናብ እጥረት በተለይ አርሶ አደሮች ምርት እንዳያመርቱ በማድረጉ ይህ አስከፊ ርሀብ መከሰቱ ነው የተገለፀው፡፡

የተባበሩት መንግስታትም  በሶማሊያ በዝናብ እጥረት ምክንያት የተፈጠረውን ድርቅ ለመቋቋም እና ዜጎችን ለመታደግ እንዲቻል ነው ለእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች እና ሀገራት ጥሪውን እያቀረበ የሚገኘው፡፡

በአፍሪካ ቀንድ ከመጋቢት መጀመሪያ እስከ ግንቦት ወር መጨረሻ የሚከሰተው የዝናብ እጥረት በቀጠናው የሰብል ምርት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ያሳድራል፡፡ በሶማሊያ የተከሰተወውም ይሄው ነው፡፡

የመንግስታቱ ድርጅት በሪፖርቱ  እንደጠቀሰው ከሆነ ደግሞ በአሁኑ ሰዓት ሁለት ሚሊዮን ሶማሊያዊያን አስቸኳይ እርዳታ ካላገኙ በርሀብ እንደሚሞቱ ነው፡፡

ይህ ቁጥር ደግሞ ከሀገሪቱ ጠቅላላ የህዝብ ቁጥር አስራ ስምንት በበመቶው እንደማለት ነው፡፡

የአለም የምግብ ድርጅት ፋኦ ደግሞ በአፍሪካ ቀንድ በዚህ አመት የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ዜጎች ከባለፈው ሁለትና ሶስት አመታት በ40 በመቶ መጨመሩን ነው ያስታወቀው፡፡ ፋኦ ለዚህም እንደምክንያት ያስቀመጠው የዝናብ እጥረትን ነው፡፡

በሶማሊያ በተከሰተው ርሀብ በአብዛኛው ህፃናት የችግሩ ሰለባ የሆኑ ሲሆኑ ከርሀብ ባለፈ ለተለያዩ በሽታዎች እየተጠቁ እንዳለም ነው የተጠቆመው፡፡

በሶማሊያ የተከሰተው ድርቅ ባስከተለው ርሀብ የአለም  ምግብ ድርጅት ፋኦ የምግብ እርዳታ ለማድረግ እንቅስቃሴ ላይ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ደግሞ ይህንን የሰብዓዊ ቀውስ ለማሰቆም ጥሪውን አስተላልፏል፡፡/ሲጅቲኤን/