ኬንያ ውስጥ በተከሰተ ግጭት በርካቶች ተገደሉ

በኬንያ ውስጥ ኬሪዮ በተባለው አካባቢ ለሳምንታት ባጋጠመ የሽፍቶች ጥቃትና በጎሳ ግጭት ቢያንስ 11 ሰዎች መገደላቸውንና በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ተፈናቀሉ። 
በኬንያ የስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚገኘው ኬሪዮ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተደጋጋሚ የከብቶች ዘረፋ አጋጥሟል። 
ረቡዕ እለት ምሽትም አንድ የጸጥታ ሰራተኛን ጨምሮ ሦስት የተገደሉ ሲሆን ባለፈው ሳምንትም ሰባት ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። 
ጥቃቱ በተፈጸመባቸው ሦስት አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ቀያቸውን እየተወ ከብቶቻቸውን በመያዝ ከአካባቢው እየሸሹ መሆኑም ተነግሯል። 
በሚያጋጥሙት ግጭቶች የተነሳም አራት ትምህርት ቤቶች የተዘጉ ሲሆን በርካታ መምህራንም በጥቃት ከሚታመሰው አካባቢ ወደ ሌሎች ቦታዎች እንዲዘዋወሩ እየጠየቁ ነው። 
እንደ ቢቢሲ ዘገባ በኬሪዮ አካባቢ ተደጋጋሚ የሽፍቶች ጥቃት አዲስ ነገር አይደለም። መንግሥትም ችግሩን በቁጥጥር ስር አውዬዋለሁ ቢልም በተደጋጋሚ እያገረሸ ነው። በአካባቢው በርካታ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች እንዳሉም የመንግሥት ባለስልጣናት ይናገራሉ።