ኡጋንዳ የጎዳና ልጆችን መርዳት በህግ ከለከለች

የኡጋንዳ ህግ አርቃቂዎች ለጎዳና ልጆች ገንዘብ፣ ምግብም ሆነ ማንኛውንም አይነት እርዳታ የሚያግድ ህግ አፅድቀዋል። ይህንን ህግ ተላልፈው እርዳታን እንለግሳለን የሚሉ እስከ ስድስት ወር እስራት ወይንም እስከ 330 ብር ቅጣት ይጠብቃቸዋል።
የህጉ አላማ ህፃናት ከሚደርስባቸው ወሲባዊም ሆነ የጉልበት ብዝበዛን ለመከላከል መሆኑም ተገልጿል።
የካምፓላ ከንቲባ ኤሪያስ ሉክዋጎ እንደተናገሩት ህፃናትን በህገወጥ የሚያዘዋውሩ ደላሎች እንዲሁም ህፃናትን ይዘው የሚለምኑም ሆነ እቃ የሚሸጡ ቤተሰቦችም ይቀጣሉ ተብሏል።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ ህጉ በተጨማሪም ቤት ለህፃናት ማከራየትም ሆነ በጥቃቅን ንግድ ላይ ተሰማርቶ መገኘትም ክልክል መሆኑን አስቀምጧል። 
በካምፓላ ጎዳናዎች ላይ እድሜያቸው ሰባት አመት የሚገመቱ ህፃናት ሳይቀር ሲለምኑም ሆነ እቃ ሲሸጡ ማየት የተለመደ ነው። 
አስራ አምስት ሺ የሚደርሱ ዕድሜያቸው ከሰባት እስከ አስራ ሰባት አመት ያሉ ህፃናት በካምፓላ ጎዳናዎች ላይ እንዳሉ የመንግሥት መረጃ ያሳያል።