ከሁለት አመታት በላይ በግብጽ የታሰረው የአልጄዚራ ጋዜጠኛ ከእስር እንዲፈታ ትዕዛዝ ተሰጠ

የግብጹ ፍርድ ቤት ባሳለፈው ውሳኔ ያለክስ ለ880 ቀናት የታሰረው የአልጄዚራው ጋዜጠኛ ማህሙድ ሁሴን ከእስር እንዲፈታ ትዕዛዝ ተሰጥቷል ተባለ፡፡

ምንም እንኳን ጋዜጠኛው እንዲፈታ ፍርድ ቤት ብይን የሰጠው ማክሰኞ እለት ቢሆንም አቃቤ ህግ ይግባኝ በመጠየቁ ጉዳዩ በሌላ ፍርድ ቤት ከታዬ በኋላ ይግባኙ ውድቅ በመደረጉ ሀሙስ እለት በድጋሜ ነጻ እንዲወጣ ተፈርዶለታልም ነው የተባለው፡፡ 

መቀመጫውን በኳታር ያደረገው ግብጻዊ ጋዜጤኛው መቼ ከእስር እንደሚፈታ በግልጽ የታወቀ ነገር ባይኖርም፤ ጠበቃው ጣሂር አቡል ናስር ግን በቀናት ውስጥ እንደሚፈታ ገልጸዋል፡፡

የግብጽ ህግ ጋዜጠኛው በ24 ሰአታት ውስጥ እንዲፈታ ያዛል የሚሉት የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የአረበኛው ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት ጀማል ኢድ የጸጥታ ሀይሎች እንዲፈታ የማይፈልጉትን እስረኛ ግን በሰበብ አስባቡ እዛው እንዲከርም ማድረጋቸው በሀገሪቱ የተለመደ ተግባር ስለመሆኑ ያነሳሉ፤ ከዚህ ቀደም ለወራት የተጓተቱ ተመሳሳይ ሂደቶችን ዋቢ በማድረግ፡፡

ከጎርጎሮሳውያኑ 2016 ጀምሮ ያለምንም ክስና የጥፋተኝነት ብያኔ በእስር ላይ የቆየው ሁሴን የሀገሪቱን ተቋማት ስም በማጥፋት እና ግጭትን የሚቀሰቅሱ የሀሰት ዜናዎችን አሰራጭተሀል በሚል ነው ለእስር የተዳረገው፡፡ ይሁንና ውንጀላውን ሁሴንም ሆነ አልጄዚራ ሲያስተባብሉ ቆይተዋል፡፡

በግብጽ ውስጥ በትንሹ ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች ያለአንዳች ክስ በፖለቲካ ጉዳዮች ብቻ እስር ላይ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩት ሰዎች ሕጋዊውን የ2 ዓመት ቅድመ ችሎት ጊዜ አልፈዋል፡፡

የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ መስራችና የቀድሞ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ ሞርሲ በ2013 ከስልጣን ከተወገዱ ወዲህ የአልጀዚራውን የመረጃ አውታር ግብፅ ብሔራዊ ጠላቴ ነው ስትል ስለመፈረጇም ነው የሚነገረው፡፡

በተመሳሳይ አመትም አብዱላህ ኤልሻሚይ፣ ባህር ሞሀመድ፣ ሞሀመድ ፋህሚይ እና ፒተር ግሬስት የተሰኙ የአልጄዚራ ጋዜጠኞች የሀሰት ዜናዎችን አሰራጭታችኋል በሚል ለእስር ተዳርገው እንደነበር ይታወሳል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን በጎርጎሮሳውያኑ 2019 ባወጣው የፕረስ ነጻነት መለኪያ ግብጽን ከ180 ሀገራት ውስጥ 163ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል፡፡ (ምንጭ፡-አልጀዚራ)