በዲሞክራቲክ ኮንጎ በተከሰተ የጀልባ መስመጥ አደጋ የ30 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለጸ

በምዕራባዊ ዲሞክራቲክ ኮንጎ በጀልባ መስመጥ አደጋ ቢያንስ የ30 ሰዎች ህይወት ማለፉና በርካቶች ሳይጠፉ እንዳልቀረ የአገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡

አደጋው የተከሰተው ሎካንጋ በምትባል መንደር አቅራቢያ በሚገኘው የማኢ-ንዶምቤ ሐይቅ ላይ ነው ተብሏል፡፡

እስካሁን ድረስ የ12 ሴቶች፣ የ11 ህጻናት እና የ7 ወንዶች በድምሩ 30 አስክሬኖች ለማግኘት መቻሉን የኢንኖጎ ከንቲባ የሆኑት ሲሞን ምቦ ዌምባ ተናግረዋል፡፡

በጀልባዋ ምን ያህል ሰዎች እንደነበሩ ባይታወቅም ከአደጋው 170 ሰዎችን በህይወት ለማዳን ተችሏል፡፡

በአገሪቱ ያሉ ጀልባዎች በአብዛኛው ከአቅም በላይ መንገደኞችን እና እቃዎችን እንደሚጭኑ ተገልጿል፡፡

በምስራቃዊዉ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ባለፈው ወር በተመሳሳይ አንድ ጀልባ ኪቪኡስ በተባለ ሀይቅ ሰምጣ በርካታ ሰዎች መሞታቸው ተጠቅሷል፡፡ (ምንጭ፡-አልጀዚራ)