የአለም ጤና ድርጅትና የጃፓን መንግስት ለደቡብ ሱዳን የአንቡላንስ ድጋፍ አደረጉ

የአለም ጤና ድርጅትና የጃፓን መንግስት በደቡብ ሱዳን ያለዉን የጤና ሁኔታ ለማሻሻል የሚያስችሉ ስድስት የአንቡላንስ ተሸከርካሪዎች ድጋፍ አደረጉ።

የደቡብ ሱዳን የስድስት አመታቱ የእርስ በእርስ ጦርነት ከግማሽ ሚሊየን በላይ ዜጎችን ለሞት ከ4 ሚሊየን በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ለስደት ዳርጓቸዉ፣ ሀገሪቱ በዘመናዊ የሰዉ ልጆች ታሪክ አስከፊ የሚባለዉ ቀዉስ ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል።

ሞትና ስደቱ ሳይበቃ በርካታ የሀገሪቱ ሴቶች ለወሲባዊ ጥቃት መዳረጋቸዉም ሌላዉ የስድስት አመቱ የሰቆቃ ታሪክ ነዉ።

በፈጣሪ ቸርነትም ሆነ ድል ቀንቷቸዉ ከሞትና ስደት የተረፉት ዜጎች ደግሞ በምግብ እጥረትና በሌሎች ሰብዓዊ ቀዉሶች አበሳቸዉን አይተዋል።

ይህንን ተከትሎ በሀገሪቱ ያለዉ የጤና አገልግሎት ደካማ በመሆኑ በርካቶች ሞተዋል።

ታዲያ ይህንን ችግር ለመቅረፍና በሀገሪቱ ያለዉን የጤና ተደራሽነት ለማሳደግ በርካታ አለም አቀፍ ተቋማትና ኃያላን መንግስታት የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።

የአለም ጤና ድርጅትና የጃፓን መንግስትም ይህንኑ አላማ የሚደግፍ እርዳታ ማድረጋቸዉ ተሰምቷል።

ለደቡብ ሱዳን የጤና ሚኒስቴር ተላልፈዉ የተሰጡት አንቡላንሶች በሀገሪቱ ገጠራማ አከባቢዎች በበሽታ ለሚሰቃዩና በትራንስፖርት እጥረት ህክምና ማግኘት ላልቻሉት ደቡብ ሱዳናዊያን እፎይታን የሚሰጥ ነዉ ተብሏል።

በአለም ጤና ድርጅት የቀጠናዉ ዳይሬክተር ዶ/ር ማሺዲሶ ሞኤቲ ድጋፉ የሀገሪቱን የጤና ዘርፍ የሚያሻሽልና ህፃናትና ሴቶችም የተሻለ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ነዉ ብለዋል።

በደቡብ ሱዳን ህፃናትና ሴቶች ለከፍተኛ የጤና እክሎች ይዳረጋሉ። አሁን ላይ ከ10ሺ እናቶች 789ኙ በወሊድ ወቀት ይሞታሉ፤ ከ1ሺ ህፃናትም 84ቱ በወሊድ ወቅት ህይወታቸው ያልፋል።

በአለም ጤና ድርጅትና በጃፓን መንግግስት የተለገሱት አንቡላንሶች ለአራት የደቡብ ሱዳን ሆስፒታሎች የሚከፋፈሉ ሲሆን ይህም የሆስፒታሎቹን የጤና አገልግሎት ቀልጣፋ ከማድረጉም ባለፈ ለበርካታ የሀገሪቱ ዜጎች የጤና ዋስትና የሚያጎናፅፍ ይሆናልም ተብሏል፡፡/ ክማ አፕዴትስ/