በኬኒያ ጋሪሳ ዩኒቨርስቲ ለ148 ህይወት መጥፋት ተጠያቂ የተባሉ ሶስት ሰዎች ተፈረደባቸው

ሶስት ግለሰቦች የዛሬ አራት ዓመት በኬንያ ጋሪሳ ዩኒቨርስቲ ከደረሰው ጥቃት ጋር በተያያዘ ተከሰው ፍርድ ተበይኖባቸዋል።

ራሺድ ቻርልስ ምቤሬሶ፣ ሞሐመድ ዓሊ አቢካር እና ሃሳን ኤዲን ሃሳን የተሰኙት እኒህ ግለሰቦች የጋሪሳውን ጥቃት ካቀነባበሩ መካከል ናቸው ተብለው ነው ፍርድ የተሰጠባቸው።

አራት የታጠቁ ሰዎች ጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ገብተው 148 ተማሪዎችንና ሠራተኞች ነፍስ ያጠፉት በጎርጎሳውያኑ 2007 ላይ ነበር።

ግለሰቦቹ የአል-ሸባብ አባል ናቸው በሚልም ነው ፍርድ የተሰጠባቸው። አራተኛው ተከሳሽ ግን ነፃ ሆኖ በመገኘቱ ሊለቀቅ እንደቻለ ታውቋል።

ነፃ የወጣውን ግለሰብ ጨምሮ ሶስቱ ግለሰቦቹ ኬንያውያን ሲሆኑ፣ ራሺድ ቻርልስ የተባለው ግለሰብ ታንዛኒያዊ እንደሆነ ታውቋል።

ራሱን የአል-ቃይዳ ክንፍ አድርጎ የሚቆጥረው አል-ሸባብ እ.አ.አ 2007 ላይ ለተከሰተው የጋሪሳው ጥቃት ኃላፊነት መውሰዱ አይዘነጋም።

በጎርጎርሳውያኑ አቆጣጠር 1998 ላይ አል-ቃይዳ የአሜሪካን ኤምባሲ አጋይቶ 200 ሰዎች ካለቁበት ክስተት በኋላ ሁለተኛው አሰቃቂ ጥቃት ነው የጋሪሳው እልቂት።

የቢቢሲው ኢማኑዔል ኢጉንዛ ፍርዱ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረ ነው ይላል፤ ከጥቃቱ ለተረፉ ትልቅ ትርጉም እንዳለው በመጠቆም።

ለአራት ዓመታት ያክል የቆየው የፍርድ ሂደት የኬንያውያንን በተለይ ደግሞ ከጥቃቱ የተረፉትን ልብ አንጠልጥሎ የቆዬ እንደነበር ነው ኢጉንዛ የሚያስረዳው።

መጋቢት 24/2007 ላይ በጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሃገር አማን ብለው ሳለ የደረሰው ጥቃት ጥበቃዎችን፣ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችና ሠራተኞችን ጨምሮ የ148 ሰዎችን ነፍስ ቀጥፏል። 500 ገደማ ተማሪዎች ደግሞ ጥቃቱን በመሸሽ ማምለጥ ችለዋል። 97 ግለሰቦች ደግሞ ክፉኛ አደጋ ደርሶባቸዋል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)